አቶ አሰፋ በቀለ ቤተሰባቸውን ጨምሮ ነዋሪነታቸው በሲድኒ - አውስትራሊያ ነው።አጭር ግለ-ታሪካቸውን ከትውልድ ቀዬአቸው ድሬ-ወሊሶ ጋር አጣቅሰው፤ የአገረ ግሪክ ቆይታና የአውስትራሊያ ሠፈራቸውን አያይዘው ያወጋሉ።
የአቶ አሰፋ እናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው በአማጭ-ረማጭ ለጋብቻ በመዳረጋቸው ደስተኛ አልነበሩምና የመጀመሪያ ልጃቸውን ትንሹን አሰፋና ባለቤታቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ ገብተው ነበር።
ጥቂት ቆይተው ግና ወደ ወሊሶ ተመልሰው የመጀመሪያ ልጃቸውን ትንሹን አሰፋ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ዘለቁ። ይሁንና አዲስ አበባ የገጠሩን ልጅ አሰፋን ፈተነች፤ ችሮታዋንም ለገሰች። የግሪክ አገር የነጻ ትምህርት ዕድልን እነሆኝ አለች።
ወደ ግሪክ አገር ሲሔዱ ትልማቸው ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ለማጥናት ነበር። ይሁንና በአባታቸው ግሪካዊ፣ በእናታቸው ኢትዮጵያዊ በሆኑ አንድ ግሪካዊ ፕሮፌሰር ምክረ ሃሳብ ሳቢያ በማዕድን ምሕንድስና በዲግሪ ተመረቁ። ሲልም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አገኙ።
ግሪክ የሙያ ስልጠና ብቻ ሳይሆን የሕይወት ተጋሪም አገጣጥማ ሰጥታቸዋለች። ዛሬም ድረስ ከአራት አሠርት ዓመታት በላይ አብረው በፍቅርና በትዳር በመኖር የልጅ ልጆች ድረስ በጋራ ለማየት ካበቋቸው ወይዘሮ ዓለም ጋርም የተገናኙት እዚያው ግሪክ ነው።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ቁርስ ቀምሰው ምሳ ሳይበሉ ያደጉባት ብትሆንም፤ ዛሬም ድረስ “ታላቅና ወርቅ አገር” ብለው ነው የሚጠሯት። ምኞታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረ የለውጥ ሂደት ለስኬት እንዲበቃ ነው።
እርግጥ ነው፤ ከመላው ቤተሰባቸው ጋር ውለው ለሚገቡባት አውስትራሊያ ያላቸው ፍቅርም ብርቱ ነው።