ደሴት አበበ፤ በቤተሰብ ሕይወቷ የሁለት ሕጻናት ልጆች ናት።በሙያ ክህሎቷ - ሕግ፣ ሰብዓዊ መብቶችና ፖለቲካ ሳይንስ አጥንታለች።በአንቂነቱ - በሴቶች መብቶችና የጾታ እኩልነት ላይ ታተኩራለች።
ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ተከትለው የተቀሰቀሱ ግጭቶችና ሰፍነው ያሉ ውጥረቶች ስጋትን አሳድረውባታል። ከራሷ ይልቅ ለራሷ ሁለት ሕጻናትና ለመላው ኢትዮጵያ ዕምቦቃቅላ ልጆች።
እናም የአንቂነት ነጠላዋ ላይ “የአገራችን ዕጣ ፈንታ፤ የልጆቻችን ዕጣ ፈንታ ነው” የሚል አሰባሳቢና አሳሳቢ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቃሎችን ማስተጋባት ጀምራለች።
ጥሪዋን የሰሙ፤ ስጋ የሚጋሩ ሁሉ ላልሰሙ እንዲያሰሙላት ታበረታታለች። ትማጸናለች።
ተማፅኖዋ ለወላጆችና ዜጎች ነው።
ማሳሰቢያዋ - ያላንዳች ዕሳቤ በማኅበራዊ ሚዲያ ጣቶቻቸው ፈጥነው ለሚተይቡቱ ነው።
ምክረ ሃሳቦቿም - “የጥላቻ ቃላቶችን አናስፋፋ፤ የኢትዮጵያ ገላ ስስ ነው” ባይ ናቸው።
በተለይም - የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቃላቶቻቸው ከሰላም መንገድ ይልቅ ስለትን ከአፎቱ የሚያወጣ እንዳይሆን አበክራ ማስገንዘብ ትሻለች።
ከቶውንም መልዕክቶቿ “ለግጭቱም ለሰላሙም ቁልፍ የሚባሉ ሰዎች ዓይን ላይ እስኪደርስ ድረስ እቀጥላለሁ” በማለት የሺህ ኪሎ ሜትሮች ጉዞዋን ጀምራለች።
አያሌ አድማጭ ጆሮዎች፣ ለሕጻናት ሩህሩህ ልቦችና ብስል አዕምሮዎች ያሏቸው ወገኖቿ መጪውን ትውልድ አብረዋት ይታደጋሉ ብሎ ተስፋ የማይጥል ማን አለ?