Coming Up Fri 10:00 PM  AEST
Coming Up Live in 
Live
Amharic radio
ኤስ.ቢ.ኤስ አማርኛ

"ከመጠጥ ሱስ ያላቀቁኝ የእግዚአብሔር እርዳታ፣ ትዳርና የልጅ አባትነት ናቸው" ሔርሞን ጋሻው

Eden Roma (L), and Hermon Gashaw (R). Source: H.Gashaw and E.Roma

"አብረን ድል አድርገናል። እሱ የወደፊት ሕይወቱን እኔ ባሌን፣ ፍቅሬን የራሴ አድርጌ ድል አድርጌያለሁ" ኤደን ሮማ

"ጠጪ ያርፋል እንጂ አይተውም"

ሔርሞን ጋሻው ከሁለት ሳምንታት ሕክምና በኋላ ከሆስፒታል ወጥቷል።

በመኪና አደጋ የእግሩ መጎዳት ከመጠጥ ሱስ ለመላቀቅ ቆሞ የማሰቢያ ጊዜ ሰጥቶታል።

ከውሳኔ ላይም ደርሷል።

በሕይወት ውስጥ ቃለ ነቢብና ግብር ተቃርነው ይቆማሉ። ፈታኝ መሰናክሎችን ማለፍ ሲቻል ግና ዕውን ይሆናሉ።

ሔርሞን ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ማገገም ጀመረ።

ዳግም ወደ መጠጥ እንደማይመለስ ለአጣጭ ጓደኞቹ አስታወቀ። 

የእነሱ ፌዝ ለበስ ምላሽ ግና "ጠጪ ያርፋል እንጂ አይተውም" የሚል ነበር።

ያሉት ደረሰ። ሔርሞን ሱሱ አገርሽቶ ወደ መጠጥ ዓለም ተመለሰ። 

ኤደንም በየመጠጥ ቤቱ እየተከተለች እስከ ውድቅትና ንጋት አብራ ማምሸትና ማደር ጀመረች።

እሱ አልኮል ያለ ገደብ ሲጠጣ፤ እሷ ውኃ እየተጎነጨች። የመጠጥ ቤት ወንበሮች ላይ እያሸለበች።

የኅሊና ሙግትና ፀሎት

ሔርሞን ከሆስፒታል ሕይወቱ በኋላ ጥቂት ቆይቶ መጠጥ በመተውና ባለመተው መካከል መዋለል ጀመረ።    

ሲልም፤ እግዜሩን ሞገተ።

"እኔ ወደ አንተ ስመጣ እንዴት ትሸሸኛለህ? እቺ ልጅ አታሳዝንህም?" ሲል በኅሊና ፀፀት ተመልቶ የእባክህ ከእዚህ አውጣኝ ተማፅኖውን አቀረበ።

እግዜሩም ፀሎቱን ሰማ። ኤደን ፀነሰች።

Community
Eden Roma (L), and Hermon Gashaw (R).
H.Gashaw and E.Roma

ብሥራቱን ከኤደን እንደሰማ ፊቱ በዕንባ ታጠበ። ተንሰቅስቆ አለቀሰ።

በሐዘን በተሰበረ አንደበት፣ በፀፀት በደቀቀ ኅሊና፣ ለኤደንና ለፅንሱ በደማ ልብ ዳግም ተንበርክኮ ለአምላኩ ፀለየ።

"ልጅ ከሰጠኸኝ፤ እባክህን አባት አድርገኝ" ሲል ዳግም ተማፅኖ አቀረበ።

ፀሎቱ ምላሽ አገኘ።

የመጀመሪያ ልጃቸው ከነዓን ተወለደ።

መጠጥ መጣጣቱን አቆመ። መጠጥ ካቆመ አምስት ዓመታትን አስቆጠረ።

በቀን እስከ አንድ ፓኮ ሲጋራ ሲያጨስ ከነበረው ሱስም ተላቀቀ።

ሔርሞን ዛሬ ላይ ቆሞ በምልሰት ከሱስ ስለመላቀቁ ሁነት ሲያነሳ፤ የጥንካሬው ምንጮች "የእግዚአብሔር እርዳታ፣ ትዳርና የልጅ አባትነት" መሆናቸውን ይናገራል።

ፍቅር፣ ፈተናና ድል

ኤደንም በምልሰት ያለፉ የሱስና የፍቅር ትግሎቿን ስትመለከት ተስፋ ያልመቁረጧና የጥንካሬ ምንጭ ራሷን ያስገርማታል።

ሔርሞን ላይ ቤተሰቦቹ ተስፋ ቆርጠዋል። "እኛ ደክሞን የተውነው ሰው" ተብላ የሐዘኔታ ምክር ተለግሷታል።

ሔርሞን ራሱ ከመጠጥ ቤት ላውጣህ ስትለው ከቶውንም ተቆጥቶ "ሂጂ በቃ አንቺን አልፈልግሽም" ብሏታል።

ስሜቷ በእጅጉ ተጎድቶ ቤቷ ገብታ አልቅሳለች።

"እግዚአብሔርዬ እባክህን ለምንድነው እኔ እንደዚህ የሆንኩለት? ወይ እሱን ወይ እኔን ለምን አትገላግለንም?" ብላ የምሬት ተማፅኖ አቅርባለች።

ሆኖም ፍቅሯ ፅኑዕ ነበርና ተስፋ አልቆረጠችም። በቃኝ ብላ የፍቅር ቋጠሮዋን አልበጠሰችም። 

ይልቁንም "አንድ ቀን ይለወጣል፤ የልጄ አባትም ይሆናል" ብላ ፅኑዕ እምነቷን ዳግም አደሰች።

ሔርሞን ተለወጠ። ከሱስ ተላቀቀ።

ኃላፊነት የሚሰማው አባትና ፍቅሩን በፈንታው አንጠፍጥፎ የሚሰጥ አፍቃሪ፣ ተከባካቢ ባልም ሆነ።

ኤደንም "አብረን ድል አድርገናል። እሱ የወደፊት ሕይወቱን እኔ ባሌን፣ ፍቅሬን የራሴ አድርጌ ድል አድርጌያለሁ" ለማለት በቃች።   

     

 

 

Coming up next

# TITLE RELEASED TIME MORE
"ከመጠጥ ሱስ ያላቀቁኝ የእግዚአብሔር እርዳታ፣ ትዳርና የልጅ አባትነት ናቸው" ሔርሞን ጋሻው 18/03/2022 12:45 ...
ዜና 27/06/2022 04:30 ...
አገርኛ ሪፖርት - የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዲሞክራቲክ ኮንጎ አየር መንገድን 45 በመቶ ድርሻ ሊገዛ ነው 27/06/2022 10:34 ...
“ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ከ 14 በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የእግር ኳስ ስልጠናን እየሰጠን ነው :: " – አቶ እዮብ እሱባለው 27/06/2022 10:44 ...
" አላማችን ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾችን እና ዳኞችን በብዛት ማፍራት ነው ፡፡" - ወጣት ፌቨን ሙሉጌታ እና ሶስና አበበ 27/06/2022 12:39 ...
" በሜልበርን የተደረገው ሰልፍ አላማ በወለጋ በአማራ ብሄር ላይ የተደረገውን ዘር ተኮር ጥቃት ለመቃወም ነው። " - አቶ ግርማ አካሉ የአማራ ህብረት በሜልበርን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ 26/06/2022 13:03 ...
ዳባሳ ዋቅጅራ፤ ከስደት ወደ ሠፈራ 24/06/2022 15:16 ...
ዜና 24/06/2022 04:51 ...
ዳባሳ ዋቅጅራ፤ ከዘመቻ ወደ ስደት 24/06/2022 12:52 ...
ዳባሳ ዋቅጅራ፤ ከጥቁር እንጪኒ እስከ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 24/06/2022 11:32 ...
View More