አቶ ሰለሞን አስናቀ ነዋሪነታቸው ሜልበርን-አውስትራሊያ ሲሆን፤ ውልደታቸው ጎርጎራ-ጎንደር ነው።
አባታቸው የጦር ሠራዊት አባል በመሆናቸው በ1953ቱ 'የታህሳሱ ግርግር' መፈንቅለ መንግሥት ወቅት ለክብር ዘበኛ አባልነት ወደ አዲስ አበባ ተዛወሩ።
የሶስት ዓመቱ ልጅ ሰለሞንም አባቱን ተከትሎ ከእናቱ ጋር ከጎርጎራ አዲስ አበባ ዘለቀ።
አባት ብዙም ሳይቆዩ ወደ ኮንጎ ዘመቱ።
ከኮንጎ ዘመቻ መልስም የውትድርና አገልግሎት ዘመቻቸው በማክተሙ አዲስ የሲቪል ሕይወት ለመጀመር ሕፃኑን ሰለሞንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ጎንደር ተመለሱ።
የቄስ ትምህርት ቤቱን አዲስ አበባ የጀመረው ሕፃኑ ሰለሞን የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በታዳጊ ወጣት ዕድሜው አዘዞ አጠናቀቀ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጎንደር ፋሲለደስ ከወነ።
በ1970 ወጣቱ ሰለሞን ለዕጩ መኮንነት ኮርስ ወደ ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት አመራ።
በዚያው ዓመት መጨረሻ በሞተራይዝድ እግረኛ ስልጠናቸውን ጨርሰው በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተመረቁ።
ከምረቃ በኋላ ምደባቸው ፍቼ ማሰልጠኛ ሆነ።
ጥቂት ቆይተውም ወደ ደቡብ ዕዝ ተዛወሩ።
የውጭ አገራት ትምህርት ቀሰማ
ከጥቂት ጊዜያት የደቡብ ዕዝ አገልግሎት በኋላ ወደ ቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ለትምህርት አቀኑ።
በዚያም የስድስት ወራት የፖለቲካ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
ወደ አገር ተመለሱ።
ባሬ ደቡብ ዕዝ የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው እስከ 1973 ግልጋሎታቸውን አበረከቱ።
ከባሬ ወደ ሞስኮ
የባሬ ግልጋሎት ላይ ሳሉ ወደ ቀድሞይቱ ሶቪየት ኅብረት መዲና ሞስኮ ኮምሶሞል ትምህርት ቤት ሄደው ለመማር ተመረጡ።
የኮምሶሞል የወጣቶች አደረጃጀት ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ እናት ክፍላቸው ደቡብ ዕዝ ተመልሰው የድርጅት መምሪያ ውስጥ ማገልገል ጀመሩ።
ግልጋሎት ላይ ሳሉ በ1977 ዳግም ወደ ሞስኮ ለረጅም ጊዜ ወታደራዊና የፍልስፍና ትምህርት ተላኩ።
ይሁንና የወቅቱ የሰሜኑ ጦርነት እያየለ በመምጣቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገር በትምህርት ላይ ያሉ መኮንኖች ወደ አገር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ።
በወቅቱ የአራተኛ ዓመት ተማሪ የነበሩት ሰለሞን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ግድ ተሰኙ።
አገር ቤት እንደተመለሱም የሶስተኛ አብዮታዊ ሠራዊት አባል ሆነው ከ1980 እስከ 1982 አገለገሉ።
ከጦር ግንባር ወደ ስደት
የሻለቅነት ማዕረጋቸውን ለመልበስ የተቃረቡት ሻምበል ሰለሞን ለከፍተኛ መኮንንነት ማዕረግ ሳይቆዩ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በጎንደር በኩል የሱዳንን ድንበር ተሻግረው ለስደት ሕይወት ተዳረጉ።
ሱዳን ውስጥ አዲሱን የስደት ሕይወት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር ሆነው መግፋት ጀመሩ።
በሱዳኑ የስደት ሕይወታቸው ፈታኝ የሆነባቸው በሕፃንነቷ የተለዩዋት የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው ናፍቆትና ሃሳብ ነበር።
ሕይወት ሌላ ገፅታና ስጦታም አላትና በሱዳኑ የስደት ሕይወት ሁለተኛ ሴት ልጅ ለማፍራትና ቤተሰብም ለመመስረት በቁ።
እንዲያ እየኖሩ ሳሉ አውስትራሊያ ነዋሪ በሆኑ አንድ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ወደ አውስትራሊያ የመስፈር ዕድል ገጠማቸው።