ዳግም ሠፈራ በአገረ አውስትራሊያ
አቶ ሰለሞን አውስትራሊያ እንደመጡ በቅድሚያ ያረፉት ሜልበርን ከተማ ነው።
ምንም እንኳ የእሳቸው ለአገረ አውስትራሊያ ኑሮ መብቃት ማለፊያ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ቢሆንም ሱዳን ያሉት ቤተሰባቸው ጉዳይ ግና ያውካቸው ነበር።
ሜልበርን ሳሉ በአጋጣሚ አንድ የቀድሞ የሱዳን ስደት ወዳጃቸውን አገኙ።
ቤተሰባቸውን ከሱዳን ወደ አውስትራሊያ ለማስመጣት ካሹ ሥራ መያዝ እንደሚያግዝ የስደት ወዳጃቸው ምክረ ሃሳብ ለገሳቸው።
በዚያም አላበቃም ወደ ሲድኒ ከመጡ ሥራ እንደሚያሲዛቸውም ቃል ገባላቸው።
አቶ ሰለሞንም አላመነቱም። እብስ ብለው ሲድኒ ገቡ። ሥራ ያዙ።
ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ቤተሰቦቻቸው ሱዳንን ለቅቀው ሲድኒ ተቀላቀሏቸው።
በሲድኒ ቆይታቸው ወቅት ግና ትኩረታቸው የግል ኑሯቸው ላይ ብቻ አልነበረም።
የጎላ ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ ነበራቸው።
በኒው ሳውዝ ዌይልስ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።
የ2000 ኦሎምፒክ አስተናጋጂቱ ሲድኒ ከአውስትራሊያ ኑሯቸው አንዱ የማይረሳ የትውስታ ቅርስ ያፈሩባት ከተማ ናት።
የኢትዮጵያውያን የሲድኒ ኦሎምፒክ ቡድን ከድል ስኬቱ ባሻገር በአቶ ሰለሞን ላይ ያሳደረው ልዩ ስሜት አለ።
እንደ ወቅቱ ሊቀመንበርነታቸው በኒው ሳውዝ ዌይልስ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ስም ልዩ የእራት ዝግጅት በማድረግ ለአትሌቶቹ ክብር ለመቸርና የአገር ፍቅር ስሜታቸውንም በጋራ ከማኅበረሰብ አባላቱ ጋር መጋራት መቻላቸው አይረሴ የትውስታ ቅርስ ሆኗቸዋል።
ከሲዲኒ ኦሎምፒክ በኋላ እ.አ.አ በ2001 መጀመሪያ ወደ አረፉባት ሜልበርን ከተማ ጠቅልለው ተመለሱ።
የሲድኒ መሥሪያ ቤታቸው ሜልበርን ውስጥ ቅርንጫፍ ስለነበረው በቀድሞ ሥራቸው ቀጠሉ።
በ2006 ግና ባለቤታቸው የግል ንግድ ሥራ ላይ መሰማራትን መረጡ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቶ ሰለሞንም የቅጥር ሥራቸውን ትተው በግል የቤተሰብ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው አሉ።