Coming Up Fri 10:00 PM  AEST
Coming Up Live in 
Live
Amharic radio

ሉዓላዊነት፣ ውል፣ ዕውቅና፤ ጃኑዋሪ 26 ለነባር አውስትራሊያውያን አዋኪ ቀን ሆኖ ያለው ለምንድነው?

Watu washiriki katika maandamano ya "siku ya uvamizi" kwenye siku kuu ya Australia mjini Melbourne 26 January, 2018. Source: Getty

አውስትራሊያ በየዓመቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የተጀመረባትን ዕለት ጃኑዋሪ 26 ታከብራለች። የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ጅማሮን "የአውስትራሊያ ቀን" ብሎ መጥራትም አወዛጋቢ ሆኖ አለ። ለአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች ጃኑዋሪ 26 ከ1938 አንስቶ በ 'ሐዘን ቀንነት' ተቃውሞ እየተካሔደበት ነው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም ዕለቱ በ 'ወረራ ቀን' ወይም ' 'የመቋቋም ቀን' በሚል ይጠቀሳል።

የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴተኞች መብቶች ክርክርን አስመልክቶ መጠነ ሰፊ የሉዓላዊነት ግንዛቤ አለ። ሆኖም በነባር ዜጎች ቡድናት ዘንድ የተለያዩ የሉዓላዊነት አተያዮች አሉ። 

ይህ ዕውቅና፣ የቃል ኪዳን ውል፣ ድምፅ እና እውነትን አስመልክቶ የአውስትራሊያ ሕዝባዊ ክርክር መነሻ ነጥብ ነው። እኒህ ዝንቅ አተያዮች አውስትራሊያ እየተወያየችበት ያለችውን የነባር ሼጎች ዕውቅና በተለያዩ ተምሳሎች ቀርጿል።   

Australians Celebrate Australia Day As Debate Continues Over Changing The Date
Australians Celebrate Australia Day As Debate Continues Over Changing The Date
Getty Images

‘ዕውቅና’

አንዱ ዕውቅናን አስመልክቶ ከቀረቡት አማራጭ መንገዶች ውስጥ የአውስትራሊያን ሕገ መንግሥት ለናባር ዜጎች ዕውቅናን እንዲቸር መለወጥ ነው። የ2020 ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ በአያሌ የጠበብት መድረኮች፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ጥያቄዎች፣ ሕገ መንግሥታዊ ኮሚሽኖች እና የሕዝበ ውሳኔ ምክር ቤቶች፣ ከ1980ዎቹ አንስቶ በቀረቡ ሪፖርቶችና ምክረ ሃሳቦች የተደገፈ ነው።

ከእኒህ ውይይቶች ውስጥ በጣሙን ዕውቅና ካገኙት ተምሳሌቶች አንዱ ከመላ አገሪቱ የ13 አካባቢዎች የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ተወካዮች ጋር ለሶስት ቀናት ተካሂዶ በዕልባትነት የወጣው የኡሉሩ መግለጫ ነው  ‘The Uluru Statement from the Heart’ 


0:00

ዲን ፓርኪን የከልብ ዳይሬክተር፤ የኡሉሩ መግለጫ ሕዝባዊ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ፓርላማ ውስጥ ድምፅ ለማስገኘት ሕዝባዊ ድጋፍን መገንቢያ እንደሆነ ሲናገሩ፤

"የኛ ውክልና 100 ፐርሰንት የኡሉሩ መግለጫ ነው። ድምፅ፣ የቃል ኪዳን ውልና እውነት በአብዛኛው የእኛ አጀንዳ ነው። የምናገረው በዚያ መልክ ነው። የፓርላማ ድምፅ ዕሳቤ የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች ተወካዮች ፓርላማ ላይ ድምፅን ለማስተጋባት፣ በአውስትራሊያ ዲሞክራሲ ውስጥ ለመናገርና የአውስትራሊያ ሕገ መንግሥት ጥበቃን ማግኘት ነው። እናም ልክ እንደ ባለፉት አካላት ወደ ጎን ማግለል አይቻልም" ብለዋል።

‘ድምፅ’

ነባር አውስትራሊያውያንን በሕገ መንግሥት ውስጥ ዕውቅና የመስጠቱ ዓላማ ማኅበረሰባቸውን በሚያሳስቡ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ የማሳደርና ከውሳኔዎችም ላይ መድረስ የሚያስችላቸው 'ድምፅ' እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው። 

ይሁንና አንዳንዶች እንደ ነባር አውስትራሊያውያን ሚኒስትር ኬን ውያት የመሳሰሉቱ 'ድምፅ' ማግኘትን የውክልና አካል በማቆም 'ለፓርላማ ድምፅ' ከመሆን ይልቅ 'ለመንግሥት ድምፅ ' መሆን እንደሚቻል አተያያቸውን ይለግሳሉ። 

“ዕውነታው የፓርላማ ድምፅ ማግኘት ይቻላል፤ ይሁንና የመንግሥት ድምፅን ማግኘት ግና የትኛውም ሁነኛ ፓርቲ ይሁን የወቅቱ መንግሥት የሆነው ነው የንዋይ ሸምቀቆዎችን የሚጨብጡት፣ ፖሊሲዎችን ይሁን የሚሉት፣ ድንጋጌዎችን የሚሰይሙት። 

“ተፅዕኖ ልታሳድሩበት የሚገባው እሱ ነው፤ መንግሥት። የፓርላማ ድምፅ የሚመጣው በመንግሥት ድምፅ " ሲሉ።


Minister for Indigenous Australians Ken Wyatt speaks to the media during a press conference at Parliament House in Canberra, Tuesday, August 17, 2021.
Minister for Indigenous Australians Ken Wyatt speaks to the media during a press conference at Parliament House in Canberra, Tuesday, August 17, 2021.
AAP Image/Lukas Coch

ይሁንና ለባንድጃላንግ እና ኩንጋራካኗ ሴት ዳኒ ላርኪን፤ የአቶ ውያት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከማስፈር ይልቅ አንድ አካል የመደንገጉ አተያይ ከቶውንም "አለመታደል" እና "ቅር አሰኚ" ሆኖ ያገኙት መሆኑን ሲጠቅሱ፤

"በአንዲት የብዕር ጭረት ከመገለል ትድግናን ለሚያስገኝ ለፓርላማ ድምፅ ሕገ መንግሥታዊ ሕዝበ ውሳኔ አያሌ ድጋፎች አሉ። ያ በእዚህ ጉዳይ ላይ አለመጠን ለለፉት በተለይም ለአረጋውያን ያለመታደልና ቅር አሰኚ ውጤት ነው የሚሆነው" ብለዋል። 

‘ውል’

ሌላው በብርቱ ክርክር የተካሔደብት ፅንሰ ሃሳብ "ውል" ነው፤ ይህም ማለት ከእንግሊዝ አገዛዝ በፊት የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች መኖርን እና በተከታታይም በነባር ዜጎች ላይ የመሬት ነጠቃና ንብረት ወረሳን መፈጸምን ዕውቅና የሚቸር በመንግሥትና በነባር ዜጎች መካከል የሚፈጸም መደበኛ ስምምነት ነው። ለበርካቶች ልክ ኒውዚላንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳ ለነባር ዜጎቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ ብሔራዊ ውል ወይም ክፍለ አገራትና አካባቢን መሠረት ያደርጉ ውሎች (ከፓርላማ ድምፅ ይልቅ) የሉዓላዊነት ዕውቅና የእርቅና እውነት ነገራ መነሻ በመሆኑ ቅድሚያ ግብ ሊሆን ይገባል።

ለዚያም ነው  በ2017 የኡሉሩ መግለጫ ወቅት በጊዜው የቪክቶሪያ ልዑክና የጉናይና ጉንዲትጄማራዋ የአሁኗን የአውስትራሊያ ግሪንስ ለቪክቶሪያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባሏን ሊንዳ ቶርፕ ጨምሮ አንድ የነባር አውስትራሊያውያን ቡድን የስብሰባ አዳራሹን ጥለው የወጡት።


Lidia Thorpe
Senator Lidia Thorpe during a smoking ceremony at the Aboriginal Tent Embassy at Parliament House in Canberra.
Getty Images

ወይዘሪት ቶርፕ ለእያንዳንዱ ነገድ ወይም ሕዝብ አንድ አካታች የሆነ የሕገ መንግሥት ሂደት እንደሚያስፈልግ የሚያምኑ መሆኑን ሲገልጡ፤ 

"ምን እንደሚሹና ምን እንደሚፈልጉ መወሰኑ የእነሱ መብት ነው። ከሰዎች ጋር ከበሬታ የተመላበት ንግግር ማድረግ፣ መፍቀድ፣ በርካታ መሠረታዊ የማኅበረሰብ አባላትን አግልሎ የጥቂት ተጋባዦች ብቻ ሂደት ሳይሆን የሁሉም ሰዎች ወደ ጠረጴዛ መምጣት ያስፈልገናል" ብለዋል።

ሉዓላዊነትን በተመለከተ መሠረታዊ የማኅበረሰብ አባላት ቅስቀሳ ለረጅም ጊዜያት የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች ሕይወትን ለማሻሻል ብርቱ ገፊ ኃይል ሆኖ ያለ ነው።  

ለተወሰኑ የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ወጣት ቡድናት የቅኝ ግዛት መዋቅሮችን በመፃረር መልክ ሕዝበ ውሳኔን ወይም ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናን ውድቅ በማድረግ በምትኩ የውል ፅንሰ ሃሳብን ይመርጣሉ። በእነሱ አተያይ፤ የቅኝ አገዛዝ ከነባር ዜጎች ሉ ዓላዊነትና የራስን ዕድል በራስ ውርሰ መብት ጋር ይጋጫል።  

እኒህ ወጣት ቡድናት የፖለቲካ መስኩን በኢንተርኔትና ማኅበራዊ ሚዲያ እየቀረጹ ሲሆን፤ እንዲሁም የለውጥ ጥያቄዎችን በማንሳት የጎዳና ተቃውሞዎችን ያስተባብራሉ፣ ያንቀስቅሳሉ ይመራሉ። 

ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናን በመጻረር በግንባር ረድፍ ካሉቱ የአቦርጂናል አማጺያን ጦረኞች እንዲሁም ጦር በመባል የሚታወቁት ይገኙበታል። 

የጦር ቡድን አባሉ ጋሚላሬይ፣ ኩማ እና ሙሩዋሪ ሰው ቦ ስፒርየም ቡድኑ ሁሌም "ከላይ ወደ ታች አቀራረብን" እንደሚቃወም ሲናገር፤ 

“የአቦርጂናል ሰዎችን ጨምሮ የማኅበረሰብ ንግግሮች መሳዩ በትክክለኛ መንገድ እየተጉዘ ነው ብዬ አላስብም። ያ እኛ ስለራሳችን ለመወያየት የምንሻው አይደለም።  ውል ሁሌም የውይይት አካል ሆኖ ያለ ነው" ሲል ገልጧል። 


Protest against Australia Day in Melbourne
Indigenous activists and supporters protesting in Melbourne on 26 January 2019.
Getty Images

የጦር ይፋዊ አቋም ከቅኝ አገዛዝ መዋቅሮች ጋር አለመነጋገር ሲሆን፤ ሆኖም አቶ ቦ ራስን በራስ የማስተዳደር ጽንሰ ዕሳቤ ያን ስለሚፈቅድ የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች ከዚያ አንፃር የራሳቸውን ውሳኔዎች መወሰን እንደሚችሉ ይገነዘባል። 

አንዱም የእውቅና ስኬት ምን ሊመስል እንደሚችል የሚካሔድ ክርክርም አለ። 

አንቂ፣ የሕግ ባለሙያና የታዝማኒያ አቦርጂናል መሬት ምክር ቤት ሰብሳቢ፤ የፓላዋ ሰው ማይክል ማንሴል የአቦርጂናል ሰዎች ትርጉም ያለውና የይስሙላ ዕውቅና ምርጫ ማድረግ እንደሚችሉ ሲጠቁሙ፤ 

"የይስሙላ ዕውቅና የተካሔደው በ2007 ኬቨን ራድ ለተሰረቁት ትውልዶች ይቅርታ የጠየቁበት ጊዜ ነው" ብለዋል።.

አቶ ማንሴል ሁነኛ የሆነ የአቦርጂናል ዕውቅናን እንደምን ሊያስገኝ እንደሚችል ሲያብራራ፤

“ውሉ ለፌደራል ፓርላማ ቢቀረብ የተወሳሰበ ሂደት አይሆንም። የፌደራል ፓርላማው ተአማኒነት ያለው ብሔራዊ የአቦርጂናል ተወካይ አካል ማቋቋሚያ ድንጋጌ ያሳልፍ፤ ያ አካል የአቦርጂናል ማኅበረሰባት ትሩፋት ለሚያገኙባቸውን ምንጮች ክፍፍል ቅድሚያ ይስጥ”

"በሁለተኛ ደረጃ፤ የፌደራል ፓርላማው የውል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ድንጋጌ ያሳልፍ፤ የውል ኮሚሽኑ ረቂቅ ውል ይያዝ። እንደማስበው ከሆነ በእነዚህ ሁለት ነገሮች እውነተኛ በሆነ መልኩ የአቦርጂናል ሰዎችን ሕይወት መለወጥ ይቻላል" በማለት አብራርተዋል። 

የፌደራል መንግሥቱ ለአቦርጂናል ሰዎች 'ድምፅ ' እንዲፈጥሩ በብሔራዊ፣ ሪጂናል አካባቢ ደረጃ ሶስት ገዲብ አማካሪ አካላትን በጋራ አጣምሯል።

የኩንጋራካን እና ኢዋይዲጃ ሰው ፕሮፌሰር ቶም ካልማ የፌደራል መንግሥቱ ድምፅ ተባባሪ ዲዛይን ገዲብ አማካሪ ቡድን አጋር ሰብሳቢ ናቸው። 

 

 

Scenes In The Winter Light Of Australia
The red rock face of Uluru at sun set, the sacred home for thousands of years of the Yankunytjatjara and Pitjantjatjara people in the central Australian desert.
Getty Images AsiaPac

ስለ አማካሪ አካላቱ ሚናም የተለያዩ ሞዴሎችን ለፌደራል መንግሥቱ ማቅረብና ከዚያም ምን ዓይነት 'ድምፅ ' መቅረፅ እንደሚያሻ ማስወሰን መሆኑን ሲያስረዱ፤

"የውል አካላቱ አወቃቀር አለን፤ ይሁንና የእኛ ተግባር ውሎቹን ማጤን አይደለም። ስለ ድምፅ ለፓርላማ መሆኑ በጣሙን ግልጽ ነው" ብለዋል።

ሪፖርቱ ተጠናቅቆ ያለ በመሆኑ፤ የፌዴራል መንግሥቱ ዕቅድ ሪፖርቱ በካቢኔ እንዲታይና ለምክክር ቀርቦ ከምርጫው በፊት ሕጋዊነትን እንዲላበስ ማድረግ ነው። 

ድጋፍ የተቸረባቸውን ሞዴሎች አስታርቆ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ቡድናት ፕሮፌሰር ቶም የአቦርጂናል ሰዎች ፊታቸው የቀረበላቸውን ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ሲያሳስቡ፤ 

"በአሁኑ ወቅት ማድረግ ያለብን ምንድነው፤ ምን ለስኬት አብቅተናል? እንደ አቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሕዝብ የሞራል መርሃችንን ሳናጎድል ለስኬት ማብቃት የምንችለው ምንድነው?

“ድምፅ ለመንግሥት እና ድምፅ ለፓርላማ ሂደትን ለሚሹ የነባር ዜጎች ጉዳዮች ሚኒስትርን የሚደግፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አሉን፤ ያንን መጨበጥና እንደምን ትሩፋቱን መጠቀም እንደምንችል መመርመር አለብን" ብለዋል። 

ለአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ሰዎች ዕድገት ፍልሚያ ሲደረግ የቆየው አውሮፓውያን የአቦርጂናል መሬትን ከረገጡ ጀምሮ ነው። 

የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴት ማኅበረሰባት መንግሥት ዕውቅናና ድምፅን ለብሔራዊ አጀንዳነት እንዳቀረበ ከተለያዩ ሞደሎች በአውስትራሊያ ታሪክ ውስጥ ትርጉም ያለው ዕውቅናን  ለማግኘት ስሙም ናቸው። 

This story is also available in other languages.