“ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያ፤ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!”
እኒህ የሕይወትና ዘላለማዊነት፥ የብሔራዊ ማንነትና አንድነት ቃላት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተስተጋቡት በ10ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር (ከአክሊሉ ሃብተወልድ ዘመነ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አንስቶ) ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አንደበት ነው፡፡ የካቲት 24/2010 በመጀመሪያዋ የ100 ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትራዊ ጉዞ ጅማሬ ዕለት ፡፡

የበዓለ ሲመት ንግግራቸው በግዙፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ በወርቃማ ቃላቶች አሸብርቀው፣ በርቱዕ አንደበት በአገረ ኢትዮጵያ ላይ የናኙ የማለፊያ ተውኔት መነባንቦች አልነበሩም፡፡
ከቶውንም መተማ፣ ማይጨው፣ ካራ ማራና አድዋ ላይ መተኪያ የሌላት ውድ አገራቸውን ለመታደግ ሕይወት ነጥቀው፤ ሕይወት ሰጥተው፤ በቁማቸው ኢትዮጵያውያን፤ በቤዛ ሰማዕትነታቸው ኢትዮጵያን ሆነው በኢትዮጵያ ጥቁር አፈር፤ ተራሮች፥ ዱር፥ ሸንተረርና ፈፋዎች ላይ የወደቁት፤ ለውድ አገራቸው ችሮታን እንጂ ንፍገትን የማያውቁቱ አባቶችና እናቶች ልጆች ነንና ‘አደራ በል እንዳንሆን’ ያሉበት በቃለ ውበት የታጀበ ቃለ አደራ ነው፡፡
ሲልም፤ ቀደምት አባቶችና እናቶች ላንለያይ አሰናስለው፤ ላንነጣጠል አዋድደው አዋህደውናልና ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት፤ አገራችንም ኢትዮጵያ ናት የሚል ቃለ ውርስ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች” ሲሉ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን፤ ኢትዮጵያውያንም የኢትዮጵያ በመሆን የእንደመር ጥሪያቸውን ያከሉት፡፡
አገራቸውን ለታላቅነት፥ ሕዝባቸውን ለብርቱ ለውጥ ተሳታፊነት ሲያሰናዱም፤ “ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን፤ ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው” በማለት የለውጡ ጎዳና መነሻው ጋሬጣ የበዛበት፤ መድረሻው ግና የአዲስ ዘመን ትሩፋት የመላበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመጀመሪያው የ100 ቀናት አዲስ ምዕራፍ ጅማሬ ዕለት የኢትዮጵያዊነትን የፓን-አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ መሰረትነት ዋቤ ነቅሰዋል፡፡ ድንበር ተሻግረው ለኤርትራ መንግስት የጋራ ሰላምና ጥቅሞች ተጋሪ ለመሆን ልዩነቶችንና ቁርሾዎችን በውይይት እንፍታ ሲሉ ልባዊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መለስተኛ ተቃውሞ ቢያስከትልባቸውም፤ አፍ ተልብ ሆነው የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ቅናሽና ጭማሪ ሳይታከልበት ሙሉ በሙሉ ግብር ላይ ይውል ዘንድ በአካል አሥመራ ተገኝተዋል፡፡
የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂም ጦር የሰበቁባት፣ ደም የተቃቧትን የኢትዮጵያ መሪ የሚቀበሉ ሳይሆን፤ ከቶውንም ለሁለት አሠርት ዓመታት የደረሰበት ጠፍቶ ያልታወቀ ወንድማቸውን ድንገት ያገኙ ያህል በሞቀ አገርኛ ልባዊ አቀባበል እጆቻቸውን ዘርግተው፣ ልባቸውን ከፍተው “መርሓባ - እንኳን ደህና መጣህ” ነበር ያሉት፤ ዶ/ር አቢይ አሕመድን፡፡

የአሥመራ ሕዝብም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ፣ ምስላቸው ያለበትን ቲሸርት ለብሶ፥ አውቶሞቢላቸውን በፍቅር ተመልቶ በሆይታ አጅቧል፡፡ ለመኪናይቱ ቀረብ ያሉትም በአገርና በወንዝ ልጅነት ስሜት ናፍቆትና ፍቅር ቀላቅለው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉንጮች ስመዋል፡፡ ተስመዋል፡፡ መሪና ሕዝብ፤ ሕዝብና መሪ ልብ ለልብ ተገናኝተዋል፡፡
አሥመራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን በመንግስታዊ የክብር እራት ግብዣና ጥዑም ቡን ብቻ ሳይሆን ተቀብላ የሸኘቻቸው ባለ ስድስት ነጥብ የጋራ መግለጫ ላይ ፊርማዋን አኑራ ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ጦርነት ላይመለስ ማክተሙን ጭምር አውጃ ነው፡፡

በታካይነትም፤ ግልፅ የድንበር ከለላ፣ ወደቦችን ለጋራ ጥቅም ማዋል፣ የአየር መንገዶች በረራ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካ፣ የፀጥታ፣ የምጣኔ ሃብትና የማኅበራዊ በሮች እንዲከፈቱ ተስማምታለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግና ለሕዝብ - ለሕዝብ ወዳጃዊ ግንኙነቶች ዝልቀት ቃሏን ሰጥታለች፡፡
ኢትዮጵያም በበኩሏ፤ የሁለቱ አገራት ዋነኛ ቁርኝቶች መሬትና ወደቦች ሳይሆኑ፤ ህያው የሆኑ የዘመን ተሻጋሪ ትውልዶች ልዩ ልባዊ ወዳጅነቶች ናቸው በሚል እሳቤ ይሁንታዋን ቸራለች፡፡ ይህ ብርቱ እርምጃቸውም ለሰላም የኖቤል ሽልማት ዕጩ እንዲሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የመነጋገሪያ ነጥብ ሆኗል።
እርግጥ ነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የ100 ቀናት ክንውኖች እኒህ ብቻ አይደሉም፡፡
ከመነሻው በስስትና በስጋት የተመሉ ድምፆች ‘ለእንዳልካቸው ካቢኔ ፋታ ነፍገን አብዮቱን እንዳስነጠቅነው ሁሉ፤ አሁንም ዶ/ር አቢይን ፋታ ነፍገን ይህን ሕዝባዊ ለውጥ እንዳናስቀለብስ’ ሲሉ ቢደመጡም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግና ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ተከታታይ አስደማሚና ‘አጀብ’ አሰኚ ተግባራትን በመከወን ፋታ ሲመኙላቸው የነበሩ ወገኖችን እፎይታ አሳጥተዋል፡፡
ባለፉት 100 ቀናት በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በመፍታታቸው፤ የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁን በማንሳታቸው፤ በሽብር ባሕረ መዝገብ ሰፍረው የነበሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በምሕረት አዋጅ ነፃ በማድረጋቸው ‘አበጁ’ ተብለው ተወድሰዋል፡፡

በአንፃሩም፤ እንደ አልጀርሱ ስምምነት ሁሉ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ መብራት ኃይልንና ኢትዮ - ቴሌኮምን ጨምረው በውዥቀት ላይ ያለውን ምጣኔ ሃብት ለመታደግ አምስት የሕዝብ ንብረቶችን በከፊል እሸጣለሁ፤ ወደ ነፃ ገበያ አመራለሁ በማለታቸው ‘ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይወስዱን’ የሚሉ የፕራይቬታይዜሽን ተቀናቃኝ ድምፆች ዛሬም ድረስ ተቃውሞአቸው እየተደመጠ አለ፡፡
አልፎ ተርፎም ሰኔ 16 ‘ዲሞክራሲን እንደግፍ፤ ለውጥን እናበርታ’ በሚል መሪ ቃል ምስጋናቸውን ለማቅረብ፥ ድጋፋቸውን ለመቸርና በለውጡ አካልነት ለመደመር የታደሙ ሚሊዮኖች በተገኙበት የመስቀል አደባባይ “ኢትዯጵያ የሁሉም፤ ሁላችንም የኢትዯጵያ ነን” ብለው እንዳበቁ የቦምብ ጥቃት ተቃጥቶባቸዋል፡፡ በጥቃቱ ሳቢያም የሁለት ኢትዯጵያውያን ሕይወቶች ሲቀጠፉ፤ ከ150 በላይ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
ለቦምብ ጥቃቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፀፋ ምላሽ የነበረው “የዛሬ መስዋዕትነት ለኢትዮጵያውያን ፍቅር፣ ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ለኢትዮያውያን አንድነት የተከፈለና ሁሌም የምናስታውሰው [ነው]. . . ኢትዮጵያ ከጀመረችው፣ የፍቅርና የይቅርታ መንገድ ሊገታት የሚችል ኃይል የለም” የሚል መስዋዕትነትን የዘከረና የለውጥ ሂደቱ ከፊቱ የሚደቀኑ ማናቸውንም ዓይነት ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁሞ ያልፋል የሚል የቁርጠኝነት ቃል ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በለውጥ ሂደቱ አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡንና ፈተናዎችንም መቋቋሙን ቀጥሏል።
የለውጡ ዑደት ቀጣይ ነውና ተጨማሪ አንኳር ተግዳሮቶችም ይጠብቁታል።
- የበጀት ጉድለትን ማስተካከል
- የውጭ ዕዳ ከፈላ
- ዘርን የተመረኮዘ የፌዴራሊዝም መዋቅር ክለሳ
- የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ
- ነፃ የምርጫ ቦርድ አሰራር ለውጥ
- የነፃ ፕሬስ ድንጋጌ ክለሳ
- እምቢታ ገጥሟቸው ላሉቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ዕልባት ማበጀት
- የሁሉም የሆነ ነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ፍኖተ ካርታ መንደፍ
- የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጣ (ሊብራል ዲሞክራሲ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ …?)
- መንግሥታዊ መዋቅር (የፓርላማ ሪፐብሊክ፣ ሙሉዕ ፕሬዚደንታዊ ሪፐብሊክ...?)
- በኢሕአዴግ አማራጭ ድርጅታዊ አወቃቀር ላይ መምከር (በግንባር በመጽናትና ወደ ወጥ የፖለቲካ ፓርቲነት መለወጥ)
እስከመጪው የምርጫ ዘመን (እ.ኤ.አ. 2020) እና ድህረ ምርጫ በብሔራዊ አጀንዳነት ከሚነሱቱ ጥቂቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ትኩረት የሚሹ፤ የብልህ አመራር ስኬትን ግድ የሚሉ ይሆናሉ።
ለውጥ ሂደት ነውና ፕሬዚደንት ኬኔዲ እንዳሉት በመቶ ወይም በሺህ ቀናት የሚቋጭ አይደለም። ምናልባትም እስከፕላኔታችን ፍጻሜ።

