ለውጥ ከምን? ለውጥ ለማን?

ለውጥ ወዴት ሊያመራ፣ የት ሊደርስ እንደሚችል በፍጹም እርግጠኝነት የሚያውቅ የለም። በተስፋ የተመላ ወይም በስጋት የራደ የይሆናል ግምት ከማሳደር በቀር። ለዚህም ነው፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ ስጋት የተስፋ ጥላ የሚሆነው። ጥቂት ተስፋዎች በስኬት፤ አያሌ ማለፊያ ሕልሞች በትነት የታሪክ ማኅደር ውስጥ በዋቤነት ሰፍረው ያሉት።

Change

Road to change Source: Courtesy of SSWC

The word has never had a good definition of the word liberty, and the American people just now are much in need of one. We all declare for liberty: but in using the same word, we do not mean the same thing…

                                     ~ Abraham Lincoln

 

 

እንደ አብርሃም ሊንከን አሜሪካ ሁሉ፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያም “ለውጥ” የሚለው ቃል በሚሊዮኖች አንደበት ቢነገርም ቃለ ፍቺውና ግብሩ ግና የተለያየ ነው።

እንደ ቁንጅና አድናቆተ አተያይ ለውጣዊ ምልከታውም ለየቅል ሆኖ ይንጸባረቃል።

በአንድ ወገን የለውጥ እርምጃው “በሕገ መንግሥታዊ ጥሰት፣ መፈንቅለ መንግሥታዊ ድርጊት፣ አንድን ጎሣ በሌላ ጎሣ የተካ ሹም ሽረትና የኢትዮጵያን ሕልውና ለአደጋ ባጋለጠ ክስተትነት” ይከሰሳል። ይኮነናል።

በሌላ ወገን፤ የለውጡ ሂደት ከነፈተናዎቹ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር የሚመለስበት፣ የዲሞክራሲ መሠረት የሚጣልበት፣ እውነተኛ አገራዊ አንድነት የሚቆምበትና የዘመነ ትንሣኤ ሽግግር” ተደርጎ ስስ ስጋትና ግዙፍ ተስፋን ባዛነቀ መልኩ ይታያል። ይወደሳል።

እርግጥ ነው፤ ለውጥ የአዲስ ዘመን ተስፋ እንጂ በጀምበር ጥልቀትና ስርቀት ውስጥ ገነተ - ሕይወት የሚወረስበት ረቂቅ ክስተት አይደለም።

ለውጥ ወዴት ሊያመራ፣ የት ሊደርስ እንደሚችል በፍጹም እርግጠኝነት የሚያውቅ የለም። በተስፋ የተመላ ወይም በስጋት የራደ የይሆናል ግምት ከማሳደር በቀር። ለዚህም ነው፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ ስጋት የተስፋ ጥላ የሚሆነው። ጥቂት ተስፋዎች በስኬት፤ አያሌ ማለፊያ ሕልሞች በትነት የታሪክ ማኅደር ውስጥ በዋቤነት ሰፍረው ያሉት።

በለውጥ ጉዞ ውስጥ ውብ አገራዊ ሕልም ይታለማል። ምድራዊ ገነትን ለመፍጠር ቅን ትልምና ግብ ይነደፋል። ትልምን ለግብር፣ ግብርን ለስኬት ለማብቃት ግና ለቃል ኪዳኒቱ ምድር የሚያበቃ ብልህ አመራር፣ ሕዝባዊ የለውጥ ባለቤትነት ተሳትፎንና አገራዊ ሕልምን አብሮ ማለምን ግድ ይላል።
Change
Past Future Source: Courtesy of KCG
የለውጥ ሂደት

አገራዊ ለውጥ ማዕቀፍና የጉዞ አቅጣጫው ዘርፈ ብዙ ነው። በግርድፉ ጥገናዊ፣ ሽግግራዊ ወይም መሠረታዊ እንድምታ ይኖረዋል።

ጥገናዊ ለውጥ - በተመሳሳይ ሥርዓት ውስጥ የጎደለን ሞልቶ፤ ሽንቁርን ደፍኖ በማስዋቢያ ቅብ የአሮጌውን ሥርዓት ገጽታ ከላይ አስጊጦ የሚያሳይ የ ‘አልሸሹም ዞር አሉ’ ትዕይንት ነው።

ሽግራዊ ለውጥ - በዚያው ሥርዓት ውስጥ ለአንድ ነጠላ ግዙፍ ሕዝባዊ ጥያቄ ወይም ለአነስተኛ ጉልህ ችግሮች መላ አበጅቶ ሥርዓቱን ከክስመት ታድጎ ለማስቀጠል የሚከወን ነው።

መሠረታዊ ለውጥ - ግና ከገዢው ሥርዓት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ክስተት ነው። አሮጌው በአዲስ የሚተካበት፣ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሕዝብ የለውጡና የወደፊት ዕጣ ፈንታው ባለቤት የሚሆንበት ነው።

የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደትም በከፊል ሽግግራዊና ከፊል መሠረታዊ የለውጥ ክስተትና ሂደት ውስጥ እየተጓዘ ያለ ነው።

ለውጥ ከምን?

ለውጥ ከትናንት አሉታዊ ድርጊቶች መላቀቂያና ወደ አዎንታዊ ክንውኖች የመሸጋገሪያ ድልድይ ነው።

ጉዞውም ከፍርሃት ወደ ተስፋ፣ ከጥላቻ ወደ ፍቅር፣ ከግጭትና መጠላለፍ ወደ ትብብር፣ ከመራራቅ ወደ መቀራረብ፣ ከስሜታዊነት ወደ ስክነት፣ ከፅንፍ ወደ ማዕከል ነው።

ሽግግሩም ከትናንት የታሪክ ሰለባነት ተላቅቆ፣ በዛሬ የለውጥ መድረክ ላይ ተረማምዶ ትውልድ ተሻጋሪ አገራዊ ሕልምና ሕዝባዊ ራዕይ ከአድማስ ባሻገር በጋራ መቅረፅ፤ ለአያሌ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የለውጥ ጉዞ አንዲት የመነሻ እርምጃ መሆን ነው።

ዓበይት ድርጊቶቹም ተቋማትን በመገንባትና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በመከወን ፍትሕ፣ ሰላምና ብልፅግናን በማስፈን፣ የመልካም ኑሮ ዋስትናን በመቸር ዜጎችን ለሙሉዕ ሰውነት ማብቃት ነው። የሚፈራ ሳይሆን የሚከበር መሪ መፍጠር፤ አገርንም በአጎራባች አገሮች ዘንድ የታፈረች፣ በዓለም አቀፍ መድረክም ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስጠባቂና አትራፊ ተዋናይ እንድትሆን ማስቻል ነው።

ለውጥ ለማን?

የለውጥ ምንጭ፣ ኃይልና ባለቤት ሕዝብ ነው። ምንም እንኳ ቀስቃሾች፣ ሲቪክ ቡድናት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች የለውጡ አንድ አንቀሳቃሽ አካል ቢሆኑም።

ስለምን? የለውጥ ተልዕኮ ማኅበራዊ የምጣኔ ኃብት ፍትሕን ለጉስቁሎች፣ ፖለቲካዊ ነፃነትን ለድምፀ ሰላላዎች፣ ሙሉዕ የሰብዓዊ መብቶች እኩልነትን ለመብት አልባዎች ማላበስ ስለሆነ።

ሲልም፤ መራር፣ እልህ አስጨራሽና መስዋዕትነትን ግድ በሚለው ትግል ውስጥ ለለውጥ ክሰታው ንቅናቄ ላብ፣ ደምና ሕይወትን ያለ ስስት አብዝቶ የሚከፍለው መጠነ ሰፊው ሕዝብ ነውና። እናም ለውጥ በሕዝብ፣ የሕዝብ ለሕዝብ የሚሆነው ለዚያ ነው።
Change
Opportunity Source: Courtesy of PD
የለውጥ ትሩፋቶች የማን?

ላብ ፈስሶ፣ በእሥራት ማቅቆ፣ ደም ተዋጅቶና ሕይወት ተሰውቶ የተገኙ የለውጥ ትሩፋቶች ሕዝብ ካልተቋደሳቸው፤ ሕይወት የለገሱ ሰማዕቶች ሙታን ሆነው ይቀራሉ። በእሥር ማቅቀው የወጡ የሚተርፋቸው ለስነ ልቦና ድቅቀትና ለመንፈስ ዝለት መዳረግ ነው። የሌሎች ዕጣ ፈንታም የበዪ ተመልካችነትና ስደት ይሆናል።

እርግጥ ነው፤ ከመነሻው ‘አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ?’ ሳይሆን ‘እኔ ለአገሬ ምን ላድርግ?’ ብለው ራሳቸውን ለተሻለች አገር ፈጠራ፣ ለትውልድ ተሻጋሪ በረከት፤ የታሪክ አሻራን አሳርፎ ለማለፍ ለተነሳሱቱ ግና ትሩፋት አልባነት ጉስቁልና እንጂ ጸጸት አያሳድርባቸውም።

ይትባሃሉ “ለውጥ ሂደት ነው” እንዲል፤ የለውጥ የመጀመሪያው ትሩፋት ተስፋ ነው። በረከቶቹ የሚታዩና የሚዳሰሱ፣ ሕይወትና አገርን በመልካም ለዋጭ የሚሆነው ግና በሂደት ነው። ሂደቱ አዝጋሚም፤ ከናፊም ሊሆን ይችላል። እንደ ለውጥ አራማጆቹና ተዋናዮቹ የጋራ ራዕይና የአንድነት ጉዞም ይወሰናል። ለውጡ ፈጣንም ይሁን አዝጋሚ፤ ፍሬው አጥጋቢም ይሁን የቅምሻ ፤ ከትሩፋቱ ማዕድ ቀዳሚ ታዳሚ ሰፊው ሕዝብ መሆን አለበት። የለውጡ ተጻራሪዎች እንኳ ሳይቀሩ።  ሰለባነት፣ ባዶነትና ግርታ እንዳይከሰት።

  ግማሽ ሙሉ - ግማሽ ባዶ

የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ በአንዳንድ ወገኖች ዓይን ግሎ የበረደ፤ በብዥታ የተጋረደ መስሎ ይታያል። የግርታዎቹ አንኳር አስባቦቹ ምንድናቸው?

  • የለውጡ ሂደት ረጅም ጊዜ ይፈጃል ተብሎ ሲታሰብ በድንገት ፈጥኖ መከሰት
  • የቀድሞ ጸረ መንግሥት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድናትና ቀስቃሾች መካከል የአገራዊ አጀንዳ ስምምነት አለመኖር
  • አገራዊ ራዕይና የጋራ ለውጥ አይዲዮሎጂ አልባነት (በጎሣና ኢትዮጵያዊነት አጀንዳ አራማጆች ዘንድ)
  • የተወሰኑ የጎሣ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ሃብት ያካበቱ ቡድኖች፣ ተፅዕኖ አሳዳሪ ግለሰቦች የፈለጉትን ወይም የጠበቁትን ያህል የለውጡ ትሩፋቶች አልደረሰንም በሚል ዕሳቤ ወደ ኩርፊያ ፖለቲካ ማዝመም ወይም የአገም - ጠቀም ተቃዋሚና ደጋፊ መሆን
  • የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በአዲስ የለውጥ አራማጅነትና በቀድሞው የግንባሩ መርሆዎች ‘ታማኝነት’፣ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል አፍ ተልብ ያልሆኑ ግንኙነቶች በአዝጋሚ ክስመት ጎዳና ላይ ማምራት
  • የፀጥታና ደህንነት ወይም አገር አቀፍ የሕግ የበላይነትን በኃይል ለማስፈን የሚያስከትላቸው መዘዞች ለአገራዊ አንድነት ስጋት መስሎ መታየት
  • በክልሎችና የፌዴራል መንግሥታቱ መካከል ከሩብ ክፍለ ዘመን ባለፈ ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊና ሕጋዊ ግንኙነቶቻቸው የተዛቡ አለያም ባልተጻፉ ሕጎች ሲተገበሩ የቆዩ መሆን
  • በበርካታ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ወይም በለውጡ ተዋናዮች ዘንድ የዲሞክራሲ ቃለ ነቢብ በቅንጭቡ ለታይታ ከመጥቀስ ያለፈ የአተገባበር ጥልቅ ግንዛቤና ተሞክሮ ያለመኖር
  • ዲሞክራሲን መሠረት ያደረጉ ተቋማዊ ሥርዓቶች ያለመኖር ወይም ያለመደርጀት ወይም አዲስ ተቋማትን ለመገንባት ረጅም ዓመታትን የሚፈጅ መሆን
  • በለውጡ ሂደት ውስጥ የተከናወኑ መልካም ግብሮች፣ እንቅስቃሴዎችና የወደፊት ትልሞች በመንግሥት በኩል ለሕዝብ በአሳማኝ መልኩ መሸጥ አለመቻልና ሕዝብ የለውጡ ባለቤትና ዘዋሪ ሆኖ እንዲሰማው ወይም መሆኑን ማረጋገጥ መሳን
  • የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ቃል አቀባዮች ለብዙሃን መገናኛ የመረጃ ፍሰታቸው ውሱን መሆን በፈጠረው ክፍተት ሳቢያ ከአዎንታዊ የለውጥ አተያዮች ይልቅ ለአሉታዊ የለውጥ ትችቶች መጉላት በር መክፈትና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለብቸኛ የለውጡ ገፅታና አንደበትነት መዳረግ
  • የአገር ውስጥ የመንግሥትና የግል ብዙኅን መገናኛዎች ብርቱ ብሔራዊ አጀንዳ ቀራጭና ተፅዕኖ አሳዳሪ ሆኖ አለመገኘት።
እናም ሁነቶቹ ያለ ግነት የለውጡን ገጽታ ከማደብዘዝ አንጻር ሁነኛ አስባቦች ሆነዋል ማለት ይቻላል። ሲልም፤ በእኒያ ወገኖች ዘንድ የለውጡ ትሩፋቶች ተጋሪ ያለመሆንን ወይም የተገላይነትን ስሜት በአሉታዊ መልኩ አሳድረዋል።

የለውጥ ትሩፋቶች የሁሉም - ለሁሉም እንዲሆኑ፤ በዜጎች ልብና አዕምሮ ውስጥ የለውጥ ተቋዳሽነት ስሜት እንዲያድር የለውጥ ተዋናዮችን ብቃት፣ ተአማኒነትና ታታሪነትን ይጠይቃል። ኢትዮጵያዊ የለውጥ ባለቤትነትን መንፈስ ማስረጽ ግድ ይላል።

ኢትዮጵያዊ የለውጥ ኅሊና፤ የኢትዮጵያውያን የለውጥ ትሩፋቶች ምንጭ እንዲሆን።

 

 

 

 

 


Share
6 min read

Published

Updated

By Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service