ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ፤ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር መሥራችና ለሶስት ጊዜያት ያህልም ተመራጭ ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል።

የማንበብና መጻፍን የዕውቀት ጮራ እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ እስከ 1974 ለኢትዮጵያውያን ለማዳረስ እሳቸውን አክሎ ‘የፊደል ሠራዊት’ እንዴት በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እንደተመሠረተ ያወጋሉ። በመሪነት ሚናቸው ያበረከቷቸውን አስተዋጽዖዎቻቸውን ይጠቅሳሉ። “በሕይወቴ በጣም ደስ የሚለኝ ለአገሬ ለኢትዮጵያ የሠራሁት ነው፤ ዋናውም የፊደል ሠራዊት ነው” ይላሉ።

ከዚያ ቀደም ሲል፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ዕሳቤው ተነስቶ በነበረበት ወቅት በUSAID በኩል ለፕሮጄክቱ ድጋፍ ለማድረግ የአማርኛ ፊደላትን በላቲን ለመተካት መጠየቁን ያነሳሉ። ምንም እንኳ አንዳንድ ሚኒስትራት በUSAID ቅድመ ሐሳብ ቢስማሙም፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ግና እምቢኝ በማለታቸው የአማርኛ ፊደላት በላቲን ፊደላት ሳይተኩ መቅረታቸውን ዋቤ ይነቅሳሉ።

በሃይማኖት ትምህርት ቀዳሚ የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀባይ ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው፣ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያው PhD ባለቤት፤ እንዲሁም በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የአፍሪካውያን-አሜሪካውያን ጥናቶች ዲፓርትሜንት ሲቆም የመጀመሪያው ተቀጣሪ መምህር እንደነበሩ ይገልጣሉ፡፡

ሰላምና ዕርቅን አስመልክቶም፤ እንደምን ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሰላም ሥራ ላይ እንደተሰማሩ፤ እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ ሎንዶኑ የተቃዋሚዎችና የመንግሥት የሰላም ድርድር ሂደቶች ውስጥ የነበራቸውን እንቅስቃሴዎች ያነሳሉ።
የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ግለ-ታሪክና ውርሰ አሻራ ትረካ የሚጠቃለለው በቀጣዩ ክፍል ሶስት ይሆናል።

