የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ በየካቲት ፷፮ቱ ሕዝባዊ አብዮት የትውልዳቸው አካል ሆነው በትግሉ እንቅስቃሴ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ለውጥ ለማምጣት የድርሻቸውን ለማበርከት ጥረዋል። በሂደቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ወጣቶች ክንፍ በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ወጣቶች ሊግ (ኢሕአወሊ) ተሳትፈዋል።
የሊጉ እንቃሴቃሴ ግና አብዮቱ ለወለደው አብዮታዊ ሰይፍ ዒላማ አደረጋቸው። ከቀይ ሽብር አረር ራሳቸውን ለማትረፍ ሲሉ ከአምስት ጓዶቻቸው ጋር ሆነው ወደ ጂቡቲ አመሩ።

Kebedech Tekleab Source: Courtesy of KTA
ዕጣ ፈንታቸው ግና ከስደት ይልቅ ለእሥር ዳረጋቸው። ቦሶማሊያ እሥር ቤቶች ውስጥም ከአንድ አሠርት ዓመት በላይ አሳለፉ።
ከቶውንም የእስራት ጊዜያቸው በስንኝ ቋጠሮ የአዕምሮ ማስሊያ ሆነላቸው። በመድሃኒት ፓኮ ላይ የተጠራቀሙት ማለፊያ የብዕር ጠብታዎቻቸውና ንጥር የአዕምሮ ጭማቂዎቻቸው ግዘፍ ነስተው ለሕትመት በቁ።
‘የት ነው?’ በሚል መጠይቀ ርዕስ ስር የተካተቱት ሥነ ግጥሞቻቸው ለተደራሲያን እነሆኝ ተባሉ።
ስሙር ብዕረኝነታቸውም በታላቁ ብላቴን ጸጋዬ ገብረ መድኅን ፊት ሞገስን አገኘ።

'የት ነው?' Source: Courtesy of KTA
የጸጋዬ ብዕር ስለ ከበደች የጥበብ ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ገለጠ።
“ከበደች በልጅነቷ የ11 ዓመት ስደት ግዞትና ወህኒ መክፈልቷንበሥነ-ግጥም ውስጣዊ ብርሃኗ ተቋቋመችው። ይህ ነው የቅኔ ብዕር መከፈልቷና ሚስጥሯ። ከመከራ ሕይወቷ ውስጥ በሥነ-ግጥም ብ ዕሯ እየታዘለች የሱማሌ ሕዝብን አዲስ ፍቅር ዳሰሰችበት፣ ታቀፈችበት እንጂ፤ የኢትዮጵያንና የሱማሌን ሕዝብ የባህል ድልድይ ቀመረችበት እንጂ፤ በወህኒ ዕድሜዋ የምሬት ባህር አልሰጠመችም።”

Kebedech Tekleab and Tsegaye Gebremedhin Source: Courtesy of KTA
ሥነ ግጥምና ሥነ ስዕል፤ የሕይወት ዘመን ቅርሶቻቸው ከመሆን አልፈው የማንነታቸው መገለጫ እስከመሆን ደርሰዋል።