አዲስ መጤዎች የአውስትራሊያ መሥሪያ ቤቶች መመዘኛዎችን ለመረዳት ግር ይላቸው ይሆናል። በርካታ መጤዎች አውስትራሊያን ሲረግጡ የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪካቸውን ጨብጠው ያሉ ቢሆንም፤ ከአውስትራሊያ መሥፈርት አኳያ ግና ብቁ ሆነው አይገኙም። ለመነሻ እንዲሆንዎት ጥቂት ምክረ ጥቆማዎችን ከSBS የሠፈራ መምሪያ እነሆን።
ችሎታዎን፣ ክህሎትዎንና ክውንዎችዎን በውል አጠቃሎ መያዝ አሥፈላጊ የሥራ ፍለጋ አካል ነው።
ለመነሻ ጥቂት ፍንጮችን እነሆ፤
እጥር-ምጥን አድርገው ነጥቡ ላይ ያተኩሩ
አንዳንዴ ምጥን የላቀ ሆኖ ይገኛል! የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክዎን በሚጽፉበት ወቅት ዋነኛ ረብ ያላቸውን መረጃዎች ያስቀድሙ፤ ሁሌም የሥራ ማመልከቻዎን ከሚያመለክቱት የሥራ ዓይነት ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያለው እንዲሆን ያድርጉ። ሥራውን ካገኙም በኋላ እንኳ ቢሆን፤ የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክዎን ወቅታዊ አድርጎ ማዘጋጀቱ ማለፊያ ነው ተብሎ ይመከራል።

የከወኗቸውን ተግባራት ይዘርዝሩ
ቀደም ሲል ሲሰሯቸው የነበሩትን ተግባራት መንቀስና መግለጥ ጠቃሚ ነው። ቀደም ሲል የነበርዎትን የሥራ ዓይነት በደፈናው ከመጥቀስ ይልቅ የእርስዎን ግላዊ ክህሎት አጉልቶ ያሳያልና።
አዎንታዊ ቋንቋን ይጠቀሙ
ከቶውንም በትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክዎ ላይ አሉታዊ ማጣቀሻዎችን አያንሱ ወይም የቀድሞ አሠሪዎን አሉታዊ ገጽታ አያመላክቱ። ለምሳሌ ያህል፤ "የሥራ አስኪያጄ በእጅጉ ፍትሓዊነት የጎደለው ሰው ስለ ነበር፤ ሥራዬን ለመልቀቅ ግድ ተሰኝቻለሁ።"

የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክዎን በቀጥታ ከሥራው ዓይነት ጋር ማዋደድን ይማሩ
"ለሁሉም የሚሆን ወጥ አቀራረብ" የትምህርትና የሥራ ልምድ ታሪክ አጻጻፍ ላይ አይሠራም። የአሠሪን ትኩረት ለማግኘት ሁሌም የሥራ ማስታወቂያው ላይ የሰፈሩ ቁልፍ ቃላቶችንና ዓርፍተ ነገሮችን ይጠቀሙ።
ማለፊያ አባሪ ደብዳቤ ያዘጋጁ

ጠንካራ የሆነ አባሪ ደብዳቤ ለዝርዝር ጉዳዮች ምን ያህል ትኩረትን የሚሰጡ መሆንዎን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ነው። ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ፤ ማመልከቻውን የሚልኩለትን ግለሰብ ስምና የሥራ ኃላፊነት ለማግኘት ይጣሩ። አባሪ ደብዳቤዎንና የሥራ ማመልከቻዎን ጽፈው ከጨረሱ በኋላ የሰዋሰውና የትየባ ግድፈቶች አለመኖራቸውን ያጣሩ። ከመላክዎ በፊትም የሌላ ሁለተኛ ሰው አተያይን ማግኘት መልካም ነውና፤ የጓደኛዎን ምክረ ሃሳብ ይጠይቁ።
እገዛ የሚቸሩ ነጻ ምንጮች
መንግሥታዊ፤
የአውስትራሊያ መንግሥት 'Jobactive' website የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክዎን ለማዘጋጀትና ሥራን ለመፈልግ እንደምን እገዛ ሊያገኙ እንደሚችሉ መረጃዎችንና ቪዲዮዎችን ያቀርብልዎታል።

ማኅበረሰብ፤
እንዲሁም በክልልዎ ወይም ክፍለ ግዛትዎ የሚገኝ Community Migrant Resource Centre ድረ-ገጽን ይጎብኙ፤ አዲስ መጤዎች የአውስትራሊያ መሥሪያ ቤቶች መመዘኛዎችን እንዲረዱ የሚያስችሉ Employment Ready Workshops እገዛዎችን ይሰጣሉና። እኒህ ነጻ ሆርሻዎች የቃለ ምልልስ ችሎታዎን እንዲያዳብሩ፣ የትምህርትና ሥራ ልምድ ግለ ታሪክ አጻጻፍን እንዲያሻሽሉና እንደምን ለሥራ ብቁ ሆነው ማመልከት እንዲችሉ ስትራቴጂዎችን ያስተምርዎታል።
ኦንላይን፤
ኦንላይ ላይ ነጻ professional resume writing services ሊያገኙ ይችላሉ።
እንዲሁም አያሌ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ነጻ ምሳሌያዊ የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክ አባሪ ደብዳቤ አጻጻፎችን ከኦንላይ ያገኛሉ። ለመነሻ የሚሆኑዎትን ጥቂት ድረ-ገጾች እነሆ፤

የትምህርትና የሥራ ልምድ ግለ ታሪክን ለማዘጋጀትና ሥራን ለማፈላለግ ተጨማሪ መረጃን ከዚህ በታች ካለው Jobactive ቪዲዮ ሊያገኙ ይችላሉ፤
Share

