አውስትራሊያ ዛሬ ማለዳ ኳታር ላይ ከፈረንሳይ ጋር ባደረገችው የመጀመሪያ የፊፋ 2022 የዓለም ዋንጫ ግጥሚያ 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል ተነስታለች።
የአውስትራሊያው አጥቂ ክሬይግ ጉድዊን ጨዋታው በተጀመረ ዘጠነኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋን ግብ በማስቆጠሩ የድፍን አውስትራሊያን ተስፋ ከፍ አደረገ።

"ኦዚ! ኦዚ! ኦዚ! - ኦይ! ኦይ! ኦይ" አሰኘ።
ሆኖም የዓለም ሻምፒዮና ባለ ሬኮርዶቹ የፈረሳይ ተጫዋቾች እምብዛም ሳይቆዩ ጨዋታውን በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ያዙ።
አስከትለውም በ27ኛው ደቂቃ በአድሪያን ራቢዮኽ አማካይነት የመጀመሪያ ግብ በማስቆጠር ፈረንሳይን ለአቻነት አበቁ።
በ32ኛው ደቂቃ በአሊቪይዛህሩ ጂሮድ ሁለተኛ ግብ፣ በ68ኛው ደቂቃ የጨዋታው ምርጥ ተጫዋች የተሰኘው ክያን እምባፔም አንድ ግብ፤ ከሶስት ደቂቃ በኋላ ጂሮድ ዳግም አንድ ግብ በማስቆጠር ፈረንሳይን ለአራት ግቦች ባለቤትነት አድረሰዋል።

የአውስትራሊያ በፈረንሳይ 4 ለ 1 ድል መነሳት ከስታዲየሙ ውጪ በሁለቱ ቡድናት ደጋፊዎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስና እጅ ለማሰናዘር አድርሷል።
ሳዑዲ አረቢያ
የሳዑዲ አረቢያ ብሔራዊ ቡድን አርጀንቲናን በትናንትናው ዕለት ኳታር ላይ 2 ለ 1 ድል ማድረግ ተከትሎ የአገሪቱ ልዑል አልጋወራሽ አባት ንጉሥ ሳልማን ለብሔራዊ ቡድኑ ክብር ለመቸር በአገር አቀፍ ክብረ በዓልነት እንዲከበር አውጀዋል።

ሳዑዲ አረቢያ የፊታችን እሑድ ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዋን ከሜክሲኮ ጋር ታካሂዳለች።

