የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ታህሳስ 23, 2013 “ክፋትን ተላብሶ የተዘራው ዘር መርዛማ ፍሬውን አፍርቷል” ሲል ባወጣው መግለጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ላይ “አሰቃቂና ዘግናኝ ግድያ ሲፈጸም በከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት እየተመለከትን ነው” ብሏል።
አክሎም “ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ ከእልቂቱና ከማፈናቀሉ ጀርባ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት ለእልቂቱ ተባባሪና ዋና ዘዋሪ ሆነው መገኘታቸው ነው” ሲልም ገልጧል።
አያይዞም “ለዚህ ሁሉ የዘር ፍጅት ምክንያት የሆነው ሕገ መንግሥቱና ዘርን መሠረት አድርጎ የተዋቀረው የፌደራል ሥርዓት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው እና ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያውያንን ይሁንታ ያገኘ ሕገ መንግሥትና ሁሉንም ዜጎች በመፈቃቀድ፣ በእኩልነትና በፍትኅዊነት መብታቸውን ሊያስክብር የሚችል ፌደራላዊ አወቃቀር እስካልተመሠረተ ድረስ፣ በአገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ይኖራል ብሎ ኢሕአፓ አያምንም” የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እርምጃን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥቶ አሳስቧል።
ኢሕአፓ በመግለጫው ለኢትዮጵያ ትድግና የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝቦ ለኢትዮጵያውያን ጥሪውን ሲያቀርብም “ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠሏን እንፈልጋለን የምንል ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳንውል ሳናድር ተሰባስበን በመመካከር ለአገራችንና ለዜጎቻችን ህልውና እንድረስላቸው በማለት ኢሕአፓ ዛሬም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ኢሕአፓም የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል። የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ በማወያየት እና የጋራ አቋም በመያዝ ትርጉም ያለዉ መልዕክት ለመንግሥት እንዲያስተላልፍ እንጠይቃለን” ብሏል።