የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በኅብረቱ መሪነት ለማካሔድ ያሰብውን የሰላም ንግግር ለመጀመር ጥሪውን በይፋ አቅርቧል።
የአፍሪካ ኅብረት በድርጅቱ በኩል የሰላም ንግግሩን የሚመሩ አካላትን፣ ንግግሩ የሚካሔድበትን ሥፍራ ለይቶና ቀን ቆርጦ ለተሳታፊዎች በይፋ ጥሪ ማቅረቡን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ዛሬ መስከረም 25 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይሁንና የአደራዳሪ አካላትን፣ የሰላም ንግግሩ የሚካሔድበትን ሥፍራና ቀን ይፋ አላደረገም።
የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ "የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ መንግሥት ከዚህ ቀደም ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቀ ሆኖ ተገኝቷል" በማለት ገልጧል።
አያይዞም፤ ቀደም ሲል የሰላም ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆን ይዞት ያለውን አቋም አሁንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።
በሌላ በኩል፤ የሕወሓት መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለድርጅታቸው የተላከውን የግብዣ ደብዳቤ አስመልክተው ለአፍሪካ ኅብረት በላኩት የመልስ ደብዳቤ ላይ የሰላም ንግግሩ ልዑክ ቡድናቸውን ውደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን አስፍረዋል።
አያይዘውም፤ የኅብረቱ አጀንዳ ውስጥ የተኩስ አቁም መካተት ስለመኖሩ፣ ተጨማሪ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች እንዲኖሩ ይደረግ እንደሁ፣ ለልዑካን ቡድን አባላቶቻቸው የጉዞና ደህንነት ዋስትናን አካትተው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት መካከል የሚካሔደው የሰላም ንግግር በተቆረጠለት ቀን የሚካሔድ ከሆነ እሑድ ኦክቶበር 8 ቀን 2022 / መስከረም 29 ቀን 2015 ደቡብ አፍሪካ ላይ ይከናወናል።
የሰላም ድርድሩም የቀድሞውን የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታን አክሎ ሶስት አፍሪካውያን አባላትን ባቀፈውና በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚደንትና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ልዑክ ኦሉሴጉን አባሳንጆ እንደሚመራ ተነግሯል።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታም በበኩላቸው ከአፍሪካ ኅብረት ወገን ከአባሳንጆ ጋር በሰላም ንግግሩ መሪነት ደቡብ አፍሪካ ተገኝተው የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።