አሁን የሰፈነውን ሠላም ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።
የትብብር እና የመደጋገፍ ባህሉ በቀጣይ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ለዘላቂ ልማት እና አብሮነት የህግ የበላይነት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ባለው የሠላም፣ እውቅናና ምስጋና ቀን የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ተመስገን ጥሩነህ የክልሉ የሠላም እጦት ከዓመታት በፊት የነበረው ገፅታ ሙሉ በሙሉ መለወጡን ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ “ከዚህ በፊት በምሽት እና በጠራራ ፀሐይ የጥይት ድምፅ ሲሰማ ነበር፤ አሁን ተቀይሯል፡፡ በጠራራ ፀሐይ ሰው የሚዘረፍበት፣ የሚደበደብበት፣ የሚታገትበት፣ የሚገደልበት፣ የዜጎች የመኖር ህልውና ስጋት ላይ የወደቀበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፤ አሁን ይህ ሁኔታ በሰላማዊ ከባቢ ተቀይሯል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት አምሽቶ መንቀሳቀስ በፍራቻ የተገደበበት እና ዜጎች ፀሐይ ሳትጠልቅ ቤታቸው ገብተው የሚሆነውን ለመጠባበቅ የሚሽቀዳደሙበት እንደነበረ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ነገሮች መለወጣቸውን እና ችግሮች እየተቀረፉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
“ትናንሽ ንጉሶች እና የሰፈር አዛዦች በየአካባቢው አቆጥቁጠው የጎለበቱበት፤ እንደ መንግስት ግብር ማስከፈል፣ የፈለጋቸውን መፈፀም እንደሚችሉ ተግባራዊ ልምምድ እና ማንም ሃይ የማይላቸው እንደሆነ ማሳየትም ደርሰው ነበር፤ አሁን ይህ ቀርቷል” ብለዋል አቶ ተመስገን፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ “ትናንሽ ንጉሶች” ብለው የጠቀሷቸው አካላት አልፎ አልፎ ውስን የፀጥታ እና የፖለቲካ አመራሮችን እጅ ጠምዝዘው፣ በራሳቸው ህገ ወጥ እዝ እና ሰንሰለት አስገብተው፣ የራሳቸው አገልጋይ ለማድረግም ልምምድ ውስጥ ገብተው እንደነበር አንስተዋል፡፡
ትልቁ ችግር ደግሞ የአማራ ሕዝብ ለልማትም ይሁን ለፀጥታ እየተጠቀመበት ያለውን የወል ስም እና የጀግና አርበኞች መጠሪያ የሆነውን ፋኖነት በዚህ ርካሽ እና ሕዝብ መበደያ የሚጠቀሙ መኖራቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የፋኖን ስም ካባ በመደረባቸው ሕዝቡ “ነፃ አውጪዎቻችን እንጂ በዳዮቻችን ናቸው” አለማለቱ በፍጥነት እንዲያቆጠቁጡ አግዟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እንደ ርዕሰ መስተዳደሩ ገለጻ በዚያ ቢቀጥሉ የክልሉ ሕዝብ በከፋ ይጎሳቆል ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ እውነታውን በመረዳት ከመንግስት እና ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ህግ እና ስርዓትን በማስከበር ሠላማዊ ገፅታ መገንባት አስችሏል፡፡
የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ሕዝቡ ወደ ሚፈልገው ደረጃ እንዲደርስ ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር አንድ ሆኖ መታገል ግዴታ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል፡፡ “...ዳገቱ ፈታኝ ነው፤ ግን ማለፋችን አይቀሬ ነው፤ በምንም መልኩ ወደ ኋላ አንመለሰም” ብለዋል አቶ ተመስገን፡፡
“ኢትዮጵያ ዘወትር አዲስ የሆነች መኪና ናት፤ እንደ አሮጌ መኪና ፍሬን የምትበጥስ ውሃዋም የሚፈላ አይደለችም፤ ፀንታ እና በርትታ በድል ታልፋለች ፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ ወደ ምትፈልገው ታላቅነት ለመድረስ በለውጥ ጉዞ ላይ ናት፤ ይህ የለውጥ ጉዞዋ ስንዴውንም እንክርዳዱንም ይዞ መጥቷል፤ ስንዴውን እየተንከባከብን እንክርዳዱን እያረምን መሄድ አለብን፤ በተለይ ደግሞ እንክርዳዱን ስንነቅል ስንዴው አብሮ እንዳይነቀል ከባድ ጥንቃቄ መደረግ አለበት” ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመጣውን ፈተና አልፎ ከታሰበው ሰገነት ለመውጣት ትግል ላይ መሆኑን በጥብቅ ተገንዝበው ወደ ስልጣን እንደመጡም አብራርተዋል፡፡
በመተባበር እና በመተጋገዝ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል፡፡ እናም ተከታታይ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ አሁን የመጣውን ሠላም ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የህግ የበላይነትን ማስከበር የክልል እና የፌዴራል መንግስት ተቀዳሚ ተግባራቸው በመሆኑ የትኛውም አካባቢ ለዜጎች ምቹ እንዲሆን መታገል ለነገ የማይባል ተግባር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ አብመድ እንደዘገበው።