የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሕወሓት ቡድን በምሥራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብልና በተኩለሽ አቅጣጫዎች ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የመከላከያ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቋል።
የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ዛሬ ረቡዕ በሰጠው መግለጫ "በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በመንግሥት የቀረበለትን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመተው ዛሬ ለሊት ላይ የፈፀመው ጥቃት የተኩስ ማቆም ስምምነቱን በይፋ ያፈእሰ ነው" ብሏል።
አያይዞም፤ "ሕወሓት አሁንም ትንኮሳውን የሚገፋበት ከሆነ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ" ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ፤ "የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕወሓት እያደረገ የሚገኘውን የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል" ሲልም ገልጧል።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቃት ሰንዝሮብኛል በማለት አሳውቆ የነበረው ሕወሓት አሁንም በደቡባዊ አቅጣጫ ወታደራዊ ጥቃት ተከፍቶብኛል ሲል በቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በኩል አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በአገር መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ኅብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው፤ በሱዳን አድርጎ የአየር ክልል በመጣስ በሁመራ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ወደ ትግራይ አልፎ ለሕወሓት "የጦር መሳሪያ ሊያቀበል የነበረና ንብረትነቱ የማን እንደሆነነ ያልታወቀ አውፕላን" በኢትዮጵያ አየር ኃይል ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ተመትቶ መውደቁን አስታውቀዋል።