የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አዲስ አበባ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሰብሳቢ ሙሳ ፋኪ ጋር ዛሬ ሐሙስ ሕዳር 22 ተገናኝተው ተነጋገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዋና ፀሐፊው ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክተው "ውጤታማ" ሲሉ ገልጠውታል።
ትግራይ
ፕሪቶያ ደቡብ አፍሪካ የተካሔደውን የሰላም ድርድር ተከትሎ የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን ዝርዝር ዕቅድ አስመልክቶ ሽሬ ላይ በባለ ሙያዎች የጋራ ኮሚቴ እየተመከረበት መሆኑን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የባለ ሙያዎቹ የጋራ ኮሚቴ ከትናንት ኅዳር 21 ቀን ጀምሮ ሽሬ ላይ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፤ የተውጣጣውም ከፌዴራል መንግሥቱና ከትግራይ ታጣቂዎች መሆኑ ተነግሯል።
የጋራ ኮሚቴው ዝርዝር ዕቅድ ትጥቅ የማስፈታት፣ ካምፕ የማስገባትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጧል።
ኮሚቴው በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የዝርዝር ዕቅድ ነደፋውን እንደሚያከናውን ይጠበቃል።