SBS ኦዲዮ በስርጭቱ ላይ አራት ቋንቋዎችን ሊያክል ነው።
ታካይ ቋንቋዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገረው ኦሮምኛ፣ ቫኑዋቱና ማላይ የሚነገረው ቢስላም፣ ቲሞር-ሌስቴ እና ምዕራብ ቲሞር የሚነገረው ቴተም አዲስ ስርጭት የሚጀምሩ ሲሆን፤ በደቡብ እስያ ማኅበረሰብ ውስጥ ተጠቃሚነቱ እያደገ ያለው ቴሉጉ በፓንጃቢና ኔፓሊ ቡድኖች ስር ዳግም ተስፋፍቶ ለስርጭት ይቀርባል።
በተያያዥነትም አውስትራሊያ ውስጥ የዕለት ተዕለት ኑሮና ተዛማጅነትን ለማገዝ የደቡብ እስያ ማኅበረሰብ ወጣቶች ላይ ያተኮረ የእንግሊዝኛ ስርጭት የሚቀርብ ይሆናል።
እንዲሁም፤ የነባር ዜጎች ቋንቋዎች እንዳይጠፉ ለመታደግ ስርጭት ይካሔዳል።
SBS በጥቅሉ ከ63 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የኦዲዮ ስርጭቱን ያከናውናል።
በቅርቡ ይፋ በሆነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት 5.6 ሚሊየን አውስትራሊያውያን ቤታቸው ውስጥ የሚነጋገሩት ከእንግሊዝኛ ውጪ በሆኑ ቋንቋዎች ነው።