የአውስትራሊያ ሌበር ፓርቲ መሪ አንቶኒ አልባኒዚ ፓርቲያቸው በሕዝብ ምርጫ ለመንግሥትነት ከበቃ ለአውስትራሊያውያን "የተሻለ መፃዒ ጊዜ"ን እንደሚያስገኝ አመላከቱ።
አቶ አልባኒዚ ዛሬ ሜይ 1 በምዕራብ አውስትራሊያ መዲና ፐርዝ ኦፕተስ ስታዲየም ይፋ ባደረጉት የ2022 አገራዊ ምርጫ አጀንዳቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት አውስትራሊያውያን "በ20 ቀናት ውስጥ ለተሻለ መፃዒ ጊዜ ድምፅ ትሰጣላችሁ፣ ባለ ዝቅተኛ ክፍያ ሙዋዕለ ሕፃናትን፣ ጠንካራ ሜዲኬይርንና የአረጋውያን ክብካቤ ቀውስ መክላትን ትመርጣላችሁ፣ አለያም አሁን ያለው ዓይነት በዝቶ ይኖራችኋል" ሲሉ የፌዴራል መንግሥቱን መልሶ በመምረጥና አዲስ የሌበር መንግሥትን በመመሥረት መካከል ያሉ ልዩነቶች በንፅፅሮሽ አቅርበዋል።
በሥፍራውም የቀድሞ የሌበር ጠቅላይ ሚኒስትራት ኬቨን ራድና ፖል ኪቲንግ ተገኝተዋል።

ከፕሪሚየሮች ማርክ ማጋዋን (ምዕራብ አውስትራሊያ) እና ፒተር ማሊናዩስካስ (ደቡብ አውስትራሊያ) ከታዳሚዎቹ ውስጥ ነበሩ።

አቶ አልባኒዚ በይፋ የምርጫ ዘመቻ ጅማሮ ንግግራቸው ወቅት የሌበር ፓርቲ ለመንግሥትነት ከበቃ የፆታ ክፍያ ክፍተትን ለማጥበብ፣ የአረጋውያን ክብካቤ ማኧከላት ቀውስን ለመክላት፣ የቤት ግዢና ኝባታ አቅምን ለመደጎም፣ የአውስትራሊያን ፈብራኪዎች ለመደገፍ፣ የኤሌክትሪክ መኪና በመሳሰሉ ታዳሽ ኃይል ላይ ሙዋዕለ ንዋይ ለማፍሰሰ ቃል ገብተዋል።
እንዲሁም መንግሥታቸው የመድኃኒት ወጪዎችን ለመቀነስ ለመድኃኒት ትሩፋቶች ዕቅድ መሠረት በ $12.50 ለማስቀነስ ከ $42.50 ወደ $30 ዝቅ እንደሚያስደርግ አስታውቀዋል።
አያይዘውም፤ ለሌበር መንግሥት ምሥረታ ድምፅን መስጠት ማለት "ለተሻለ መፃዒ ጊዜ ድምፅ መስጠ ነው" ብለዋል።

የሌበር የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይዋ ሴናተር ፔኒ ዎንግ በበኩላቸው ስለ ሌበር መሪ አንቶኒ አልባኒዜ ሲናገሩ "ብርቱ ተፋላሚ" እና "ሩህሩ ልብ" ያላቸው ናቸው ሲሉ ገልጠዋቸዋል።

