የሌበር የፌዴራል ምክር ቤት ዕጩ ሜሪ ዶይል ለ30 ዓመታት በሊብራል ፓርቲ ስር የነበረውን የአስተን ማሟያ ምርጫ አሸነፉ።
በአውስትራሊያ ታሪክ ውስጥ ባለፉት 103 ዓመታት በመንግሥትነት ያለ ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲ ላይ በማሟያ ምርጫ ወቅት አሸናፊ ሆኖ አያውቅም።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በሕዝብ መኖሪያ ቤት ያደጉት ሜሪ ዶይል የአስተን ምርጫ በማሸነፍ ራሳቸውንና ሌበር ፓርቲን በታሪክ ባሕር መዝገብ ላይ አስፍረዋል።
አዲሷ የአስተን ተመራጭ የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ዶይል "ለእኔ ድምፃችሁን ለሰጣችሁም ሆነ ለነፈጋችሁኝ ሁሉ፤ ሁሌም እንደማደምጣችሁ ቃል እገባለሁ። ለእዚህ አካባቢ ሁሌም አቅሜ በሚችለው መጠን ሁሉ እሠራለሁ፤ ሁሌም ይህን አካባቢ አስቀድማለሁ" ብለዋል።
ዛሬ ማለዳ ላይ ከታዝማኒያ ተነስተው ከአንዲት የአስተን ካፌ ከሜሪ ዶይል ጋር ቡና የጠጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ "ሜሪ ዶይል በምርጫ ዘመቻው ወቅት ርህራሄ፣ ክብርንና ጨዋነትን አሳይተዋል። እንደ አስተን ምክር ቤት አባልነታቸውም ትርጉም ያለው ለውጥን ለማስገኘት ይሻሉ፤ ይህን እደሚያደርጉም ፍፁም እርግጠኛ ነኝ" ሲሉ አወድሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሜሪ ዶይልን በመመረጥ ለሌበር ፓርቲ አንድ ተጨማሪ የምክር ቤት ወንበር የቸሯቸውን የአስተን መራጮችን አመስግነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በምርጫው ድል የተነሳው የተቃዋሚው ሊብራል ፓርቲ መሪ ፒተር ዳተን ፓርቲያቸው ቪክቶሪያ ውስጥ "አያሌ የግንባታ ሥራ" እንደሚያሻው ተናግረዋል።
የአስተን የማሟያ ምርጫን ለማካሔድ ግድ ያለው የቀድሞው የሊብራል ሚኒስትር አለን ታጅ የሮቦዕዳ ፕሮግራምን አክሎ በበርካታ የግልና ፖለቲካዊ ትብታብ ተከበው ከመያዛቸው ጋር ተያይዞ ፌብሪዋሪ ወር ላይ ከምክር ቤት አባልነት በመሰናበታቸው ነው።
የሊብራል ፓርቲ ከሶስት አሠርት ዓመታት በላይ ይዞት የነበረውን የምክር ቤት ወንበር በማሟያ ምርጫ ማጣት ለፓርቲው መሪ አቶ ዳተን በብርቱ ፈታኝ እንደሚሆን መነገር ጀምሯል።
ይሁንና የተቃዋሚ ቡድን መሪው ቪክቶሪያ ለሊብራል ፓርቲ "አዋኪ ገበያ ናት" ብለዋል።
ኪየቭ
አንድ የዩክሬይን ፍርድ ቤት የዝነኛውና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኪየቭ ፔቸርስክ ላቭራ ገዳም ኃላፊ ፓቨል በቤት ውስጥ እሥር እንዲቆዩ በየነ።
ፍርድ ቤቱ ከብይኑ ላይ የደረሰው የገዳሚቱ ኃላፊ ለሩስያን ወረራ ወገንተኛ ናቸው በሚል ሲሆን፤ ፓቬል ግና ለእስራቸው አስባቡ ፖለቲካዊ እርምጃ እንጂ ለሩስያ ወገንተኝነትን አሳይተው አለመሆኑን በመጥቀስ የተመሠረተባቸውን ክስ "ሐሰት" ሲሉ አስተባብለዋል።
መንግሥት የዩክሬይን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መነኮሳት ከሩስያ ጋር ያላቸውን ትስስሮሽ መሠረት አድርጎ ብርቱ ክትትል እያደረገ ሲሆን፤ ሃይማኖታዊ ግጭቱ ከጦርነቱ ላይ ተደማሪ ቀውስ ሆኗል።