የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ትንናት ጥር 24 ቀን 2015 ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉት አካላትም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከማዕከላዊ መዋቅር ውጭ ተወግዘው ተለይተው እያለ በሌላቸው ሥልጣን ወዳልተፈቀደላቸው የአገልግሎት በታዎች በመግባት በሚያደርጉት ግብ ግብ በዕምነቱ ተከታዮች፣ በማህበረ ካህናትና ምዕመናን ላይ ሁከት እየተፈጠረ ነው ሲል አስታውቋል።
መግለጫው አያይዞ "በዚሁ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያን አስቀድማ ለመንግሥት ሕግን የማስከበር እና የዜጎችን ሰላም የማስፈን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያቀረበችው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዳላገኘና በሕገወጦች ላይ የተወሰደ ምንም ዓይነት እርምጃ" አልታየም ሲል አመላክቷል።
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ አክሎም፤ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔዎቻቸው በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር በማንሳት የቀረበውን ማብራሪያ በአጽንኦት ተመልክቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንኳር አቋሞች ይፋ ማድረጉን አስታውቋል።
በዚሁም መሠረት፤
የተፈጠረውን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናው ጥሰትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚ/ሩ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት አቅልለው በመመልከት "በአሁኑ ወቅት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ጉዳይ በጣም ቀላልና በንግግር የሚፈታ ነው” ሲሉ መግለጻቸው በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡
ከዚህም አልፎ "ሁለቱም ወገን ውስጥ እውነት አለ፣ ሁለቱም አባቶቻችን ናቸው፣ ለማንም አንወግንም፤ ማንም የካቢኔ አባል እዚህ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ" የሚሉት አገላለጾች በሕግ እውቅና የተሰጣትን ቤተ ክርስቲያን እና በሕጋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተነሱትን ሕገ ወጥ ቡድኖች በአቻ እይታ ተመልክተው "ሊወያዩ ይገባል" በማለት የስጡት ማብራሪያ ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ፣ ለሕጋዊ ተቋማት መንግሥት ያለበትን የመጠበቅና ዋስትና የመስጠት ኃላፊነቱን ወደ ጎን ያደረገ፣ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በሕገ ወጥ ቡድኖች እንዲታመሱና እንዲተራመሱ ይሁንታ የሚሰጥ፣ ሕግንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ታሪክና የሀገር ባለውለታነትዋን ያላገናዘበ፣ ማብራሪያ በመሆኑ ሊታረም የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኛውም ካቢኔ በዚህ ጉዳይ እጁን እንዳያስገባ በማለት የሰጡት የሥራ መመሪያ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ሰውነት አክብረው እና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉትን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚያደርግና በሕገመንግሥቱ ለአስፈጻሚው አካል የተሰጠውን ሥልጣን የሚሽር፤ ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያበረታታ፤ የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አድራጎት በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትና የተቋማትን ደህንነት የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሕጋውያን የሆኑትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ለመፈጸም ሊያደርጉት የነበረውንና ያደረጉትን ጉዞ በፀጥታ ኃይሎች በሚደናቀፍ ከኤርፖርት ታግተውና ለሃይማኖታዊ አምልኮ የተሰበሰበውን ሕዝበ ክርስቲያንም አዝኖ እንዲበተን በማድረግ ለአንድ አንጋፋና የሀገር ባለውለታ ሊቀጳጳስ የማይመጥን እንግልትና ማዋከብ መደረጉ ሳያንስ ይባስ ብሎ ለሕገወጡ የቡድን አባላት ለአብነትም ያህል በምዕራብ ወለጋ፤ በምሥራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋና ሆሮጉድሩ ዞኖች በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የልዩ ኃይል አባላት ልዩ የፓትሮል እጀባና እንክብካቤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ተቋማት በሕገወጥ መንገድ ተደፍረው እንዲገቡ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአምልኮና የአስተዳደር ተቋማት ተሰብረው በሕገወጥ ቡድኖች እንዲወረሩ መደረጋቸው፤ ይህን ሕገወጥ አድራጎት የተቃወሙትን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት አባቶችና የአስተዳደር ሠራተኞች ለእስር እንዲዳረጉ መደረጉ፣ ሕጋዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ተሽከርካሪ መኪኖች ለማንኛውም አገልግሎት እንዳይንቀሳቀሱ፣ በክልሉ መንግሥት አመራር ተሰጥቷል በሚል እገታ መከናወኑ ሲታይ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ጥስት በመፈጸም በሃይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱንና በእርሱም ይሁንታ መፈንቀለ ሲኖዶስ እየተከናወነ እንዳለ እምነት የሚያሳድር በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልናና መብት እንዲያስከብር ንብረቶቿ በሕገወጥ ቡድኖች ከመወረር እንዲጠብቅ፣ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳትና የሥራ ኃላፊዎች ያለምንም እንግልትና የደህንነት ስጋት ተመድበው ሲሠሩባቸው በቆዩበት አህጉረ ስብከት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃና የሕይወት ዋስትና እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራር በመጣስ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈጸመውን "ሢመተ ጵጵስናና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተወግዘው የተለዩት ግለሰቦች ቀድሞውንም "ሹመቱን ፈጽመን በዕርቅ እና በድርድር አንድ እንሆናለን" በሚል ሲገልጹት የነበረውን ሀሳብ የሚያረጋግጥና አሁንም በድርድር ሃይማኖታዊ መመሪያችሁን ጥሳችሁ ቀኖናዊ ሥርዓታችሁን አፍርሳችሁ፤ አስተዳደራዊ መዋቅራችሁን ንዳችሁ ተቀብሏቸው እንደማለት የሚያስቆጥር ማብራሪያ አዘል መመሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በቋንቋ የመገልገል መብትን መንግሥት ማፈን አይችልም በማለት የተሰጠው ማብራሪያ በተመለከተ፡- እናት ቤተ ክርስቲያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪኳ እንደሚያረጋግጠው የቋንቋ አገልግሎትን በሕጎቿ እውቅና የሰጠች፣ ከዚህም አልፎ በተለይም ግለሰቦች በተደጋጋሚ በሚጠቅሱት በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የእምነት ተከታዮች የቋንቋ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየች ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአምልኮና የሥርዓት መጻሕፍቶች በኦሮምኛ ቋንቋ በማስተርጎም ለአገልግሎት ያበረከተች፣ ሕገወጥ ሹመቱን ከፈጸሙት ሦስቱ የተሻሩት ሊቃነጳጳሳት ጨምሮ በርካታ የቋንቋው ተናጋሪ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳትን በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት መድባ አገልግሎት እየሰጠች የክልሉን ተወላጆች በቋንቋቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን እውቀት ቀስመው ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆነ መንፈሳዊ ኮሌጆችን በመክፈት፤ በሁሉም አህጉረ ስብከት የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን አደራጅታ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋይ ካህናት፣ ዲያቆናትና ሰባክያነ ወንጌል አስተምራ ለአገልግሎት አሰማርታ እያለች የቋንቋ አገልግሎትን እንደተቃወመችና ለአገልግሎቱም በሯን እንደዘጋች በሚያስቆጥር ሁኔታ የተሰጠው ማብራሪያ ከእውነታቸው የራቀና የሕገወጥ ሥልጣን ፈላጊዎችን ሕገወጥ አካሄድና መግለጫ እውቅና የሚሰጥ አድራጎት በመሆኑ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ከአምልኮ ሥፍራ የመሬት ይዞታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አራት ዓመታት ከሌሎች ቤተ እምነቶች በተሻለ መልኩ ከአንድ ሚሊዮን አርባ አምስት ሺህ ካሜ ይዞታ በላይ እንደተሰጣትና ይህም የይዞታ ስፋት ለሌሎች ቤተ እምነቶች በድምሩ ከተሰጠው በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ እና አዲስ ይዞታ እንደተሰጠ ተደርጎ በማስመሰል የተሰጠው ማብራሪያ ፍጹም ስህተት እና ሕዝብን የሚያሳስት በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ ይኼውም ለቤተ ክርስቲያን ተሰጠ የተባለው ይዞታ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞውን በእጂ አድርጋ ለዘመናት ስትጠቀምበት የነበረውን ሕጋዊ ይዞታዋ እና ይሄው በካርታ ተረጋግጦ እንዲሰጥ ስትጠይቅ የቆየች ንብረቷ እንጂ እንደ አዲስ በሊዝ አዋጁ መሠረት በምደባ ያገኘችው አይደለም፡፡
መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና፣ በሕግ የተሰጣትን መብትና ጥቅም በማስከበር ሕገወጡን ድርጊት ተገቢውን እርምት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በአውስትራሊያና በተለያዩ አገራት ያሉ 22 የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤
1/ መንግሥት ህጋዊ እውቅና ካለው የቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በመስራት የቤተክርስቲያን አባቶች፣ አገልጋዮች እንዲሁም የቤተክርስቲያን ህጋዊ ህልውና እንዲጠበቅ ለሁሉም የመንግሥት አካላት ትእዛዝ እንዲያስተላልፍ፣
2/ ለህገ ወጥ ቡድኑ የሚያደርገውን ማንኛውንም ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲያቆም እንዲሁም ቁልፍ እየሰበሩ የቤተክርስቲያኗን ይዞታወችን የሚቆጣጠሩ ሰወችን ለህግ እንዲያቀርብ፣
3/ የሌላ እምነት ተከታዮች በዚህ ከባድ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እጃቸውን እንዳያስገቡ እንዲያስጠነቅቅ፣ ተላልፈው የሚገኙትን ለህግ እንዲያቀርብ፣
4/ ብፁዓን አባቶችን፣ የቤተክህነት አመራሮችን ከማሰር ከማዋከብ እንዲቆጠብ፣ ታስረው የሚገኙትንም እንዲለቀቁ እንዲያደርግ፣
5/ መንግሥት ለሽምግልና በሚል ሰበብ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ፓለቲካዊ ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም፣ ምንም እንኳን ተሰምቶ እና ተደርጎ በማይታወቅ መንገድ የሃይማኖት እና የቀኖና ጥሰት የተደረገ ቢሆንም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በይቅርታ መመለስን ክፍት ያደረገ ስለሆነ ያለመንግሥት ጣልቃገብነት ይህንኑ ሃይማኖታዊ መንገድ በመከተል ጉዳዩ እልባት ማግኘት ይችላል ሲል ለኢትዮጵያ መንግሥት ማሳሰቢያውን ልኳል።