በስልጣን ቁንጮ መንበር አስቀማጭነት ብርቱ ተፅዕኖ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ቦላ ቲኑቡ ፅኑ ፉክክር በታየበት ብሔራዊ ምርጫ አሸናፊ በመሆን የናይጄሪያ አዲሱ ፕሬዚደንት ሆነው ተመረጡ።
በምርጫው ወቅት 36 ፐርሰንት ድምፅ አሸናፊ በመሆናቸውም ከተቀናቃኞቻቸው ከቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንትና ነጋዴ አቲኩ አኩባካር እና የቀድሞው የክፍለ አገር አስተዳዳሪ ፒተር ኦቢ ጋር ለዳግም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ መቅረብን ማስወገድ ችለዋል።
ፕሬዚደንት ቲኑቡ በትረ ስልጣናቸውን ከጨበጡ በኋላ ለ220 ሚሊየን ናይጄሪያውያን ባሰሙት ንግግር የቀድሞው ፕሬዚደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ መፍታት የተሳናቸውን ምጣኔ ሃብታዊና ማኅበራዊ ችግሮችን መፍታት ቀዳሚ ውጥናቸው መሆኑን ገልጠዋል።
አቶ ቲኑቡ በናይጄሪያ መዲና አቡጃ ንግግራቸውን ባስደመጡበት ወቅት የፕሬዚደንታዊ ዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።
በሌላ በኩል ከቲኑቡ ጋር በዕጩ ፕሬዚደንት ተፎካክረው የነበሩት አኩባካርና ኦቢ የምርጫው ድምፅ ውጤት ቴክኒካዊ የሂደት ሳንካ ያለው በመሆኑ ውጤቱ እንዲመረመር የሚሹ መሆኑን አስታውቀዋል።