በብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ (ብሪክስ) የተቋቋመው አዲስ የልማት ባንክ ባንግላዴሽ፣ የተባበሩ አረብ ኢምሬትስና ግብፅን በአባልነት መቀበሉንና ሳኡዲ አረቢያና ዩራጓይ የአባልነት ማመልከቻ ማስገባታቸውን አስታወቀ።
የልማት ባንኩ ይህንን ያስታወቀው፤ በኬፕ ታውን ደቡብ አፍሪካ ግንቦት 24 እና 25 ለሁለት ቀናት የተካሔደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትሮች ስብሰባ ባለ 17 ነጥብ መግለጫ አውጥቶ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው።
የሚኒስትሮቹ ጉባኤ ባወጣው የጋራ መግለጫ፤ ፖለቲካዊና ፀጥታ፣ ምጣኔ ሃብትና ፋይናንስ፣ ባሕላዊና የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር የብሪክስ መሠረታዊ ትብብር ምሰሶዎች የሆኑት ማዕቀፎች ላይ ያለውን ፅናት ዳግም ይገልጣል ብሏል።
አያይዞም፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤትን አካትቶ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የዓለም ንግድ ድርጅትና የዓለም የገንዘብ ድርጅቶች የመዋቅርና አሠራር ለውጥ እንዲካሔድባቸው ጥሪ አቅርቧል።
ሚኒስትሮቹ በብሪክስ አባል አገራትና በሌሎችም መካከል የሚካሔደው የአገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብን በዓለም አቀፍ ንግድ መገበያያነትና የፋይናንስ ዝውውርን የማካሔድ ተግባራትን አበረታተዋል።
የሻንግሪ ላ ምክክር
ከግንቦት 25 አንስቶ በመከሔድ ላይ ያለውና በነገው ዕለት እሑድ ግንቦት 27 በሚጠናቀቀው የሻንግሪ ላ ምክክር በልዕለ ኃያላን አገራቱ ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና መካከል ውጥረት ታይቶበታል።
የቻይናው አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ሊ ሻንግፉ ከዩናይትድ ስቴትሱ አቻቸው ሎይድ ኦስቲን ጋር አንድ ለአንድ በግንባር ተገናኝተው ለመነጋገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል።
ሎይድ ኦስቲን ከሲንጋፖሩ አቻቸው ጋር ተነጋግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር በኮቪድ 19 በመያዛቸው ሳቢያ በእግራቸው የተተኩት ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሎረንስ ዎንግ፤ በሻንግሪ ላ ምክክር ላይ ታድመው የአውስትራሊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በንግግር ካስደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን አገራት ስትራቴጂያዊ የቀጣና ግንኙነት በማስመልከት ተነጋግረዋል።
አቶ ዎንግ የፀጥታ ስትራቴጂ ምክክሩን አስመልክተው በርካታ የእስያ አገራት ተገድደው ከዩናይትድ ስቴትስ ወይም ከቻይና ጋር መወገንን እንደማይሹ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
አክለውም፤
"የቻይናን ዕድገት ደፍቆ ለመያዝ ወይም የአሜሪካን በቀጣናው መገኘትን በመገደብ ወገንተኝነት ዘርፍ መቆም የሚሻ ማንም የለም። በዚህ ቀጣና እንዲያ ባለው አቅጣጫ የመጓዙ ሁኔታ ተቀባይነት ያለው በጥቂቶች ዘንድ ብቻ ነው። የደቡባዊ እስያ አገራት ማኅበር ዘንድ አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነትን ማየት የሚሻ የለም" ብለዋል።
በሲጋፖሩ ስትራቴጂያዊ ምክክር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒዚ በ50ኛው የአውስትራሊያና ቬይትናም ዲፕሎማሲያዊ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ከሲንጋፖር ወደ ቬይትናም አቅንተዋል።