የአውስትራሊያ ብሔራዊ ባንክ የአገር አቀፍ ምርጫው ከመካሔዱ ሶስት ሳምንት በፊት የወለድ መጠንን በ 0.35 ፐርሰንት ጨመረ።
የብሔራዊ ባንክ በምርጫ ዘመቻ መካክል የወለድ መጠን ሲጨምር ከ2007 ወዲህ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
የወለድ መጠን ጭመራው የአውስትራሊያ ግሽበት በማርች ሩብ ዓመት ላይ ወደ 5.1 ፐርሰንት ካሻቀበ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው።
የሌበር ፓርቲ የብሔራዊ ባንክ ወለድ ጭማሪን ተከትሎ አውስትራሊያ ሙሉ የኑሮ ውድነት ቀውስ ውስጥ መሆኗን አመላክቷል።
የሌበር ዐቃቤ ንዋይ ቃል አቀባይ ጂም ቻልመርስ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን መልካም መልካም ለሆኑ ነገሮች ራሳቸውን ያወድሳሉ፤ እንዲህ ያለ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ሲመጣ ግና ራሳቸውን ከኃላፊነት ያሸሻሉ በማለት ትችተዋል።
አያይዘውም 'በስኮት ሞሪሰን አመራር ወቅት የዋጋ ግሽበት ሰማይ ነክቷል፣ የወለድ መጠን አሻቅቧል፣ የሸማቾች አመኔታ አሽቆልቁሏል፣ የደመወዝ ጭማሪ ቁልቁል ወርዷል። ይህ የዛሬው የወለድ መጠን ጭማሪ በሚሊየን አውስትራሊያውያን ቤቶች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በበኩላቸው የምጣኔ ሃብት አስተዳደራቸው ላይ ለተሰነዘረባቸው ትችት ሲመልሱ፤ አውስትራሊያውያን ላይ ብርቱ ተፅዕኖ እንዳይደርስ ለመከላከል መንግሥታቸው "ጋሻ" ማበጀቱን ተናግረዋል።
አክለውም "በዚህ ዓመት የበጀት ምጣኔ ሃብታዊ ዕቅድ መሠረት ለኑሮ ውድነት ማርገቢያ ድጎማ በማድረግ ጋሻ አበጅተናል፤ ይህን ጋሻም በወረርሽኙ ወቅት ተጠቅመንበታል" ብለዋል።