የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያ ኧፕ ቲክቶክ ከመንግሥት ስልኮችና ኮምፒዩተሮች እንዲነሳ ወሰነ።
ለጋራ ብልፅግና መንግሥቱ ውሳኔ አስባብ የሆነው በቲክቶክ በኩል የሚሰበሰቡ ዳታዎች ወደ ቻይና መንግሥት እጅ ይገቡ ይሆናል ከሚል የደህንነት ስጋት ጋር ተያይዞ ነው።
ሆኖም፤ የግሪንስ ፓርቲ የፌዴራል መንግሥቱ በቲክቶክ ላይ የጣለውን ዕቀባ በፖለቲካ ተውኔትነት ፈርጆታል።
የግሪንስ ዲጂታል መብቶች ቃል አቀባይ ዲቪድ ሹብሪጅ ቲክቶክ ላይ የተጣለው ዕቀባ ብርቱ የማሻሻያ እርምጃ እንዳልሆነ፣ የሳይበር ሴኩሪቲ ስጋት በእያንዳንዱ ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ውስጥ እንዳለና የዳታ ጉዳዮችም አማዞን፣ ሜታና ፌስቡክንም እንደሚያካትት ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ባንክ
የአውስትራሊያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 26 / ኤፕሪል 4 ባካሔደው ወርሃዊ ስብሰባው የወለድ መጠን ላለመጨመር ውስኖ ተነስቷል።
ብሔራዊ ባንኩ ካለፈው ዓመት ወርኃ ሜይ አንስቶ በተከታታይ የወለድ መጠኖችን ሲጨምር ቆይቷል።
የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ፊሊፕ ሎው ባወጡት መግለጫቸው የወለድ መጠኑ አሁን የሚገኝበት 3.60 ፐርሰንት ቀደም ሲል የተጨመሩ የወለድ መጠኖችን ተፅዕኖ ለመገምገም ጊዜ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
የፌዴራል መንግሥቱም በበኩሉ ብሔራዊ ባንኩ በዛሬ ወርሃዊ ስብሰባው ተጨማሪ የወለድ መጠን ላለመጨመር መወሰኑን በመልካም ጎኑ ተቀብሎታል።