የአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሐምሌ 27 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፃፉት ደብዳቤ ክልሉ "በመደበኛ ሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሁኔታ" ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ባጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተፅዕኖዎች ማስከተሉን ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድር "የኢፌዴሪ መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ" ሲሉ የፌዴራል መንግሥቱን እገዛ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂ ኃይሉ ፋኖ፣ የሚሊሺያና የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ግጭቶች እየተካሔዱ እንደሚገኙ የተለያዩ ምንጮች እየገለጡ ነው።
የዓለም ዋንጫ
በአውስትራሊያና ኒውዚላንድ አስተናጋጅነት እየተካሔደ ባለው የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ የመጨረሻውን የምድብ ማጣሪያ ውድድር ከፈፀሙት ውስጥ አፍሪካዊቷ ሞሮኮና ጃፓን ለጥሎ ማለፍ የሚፋለሙት 16 ቡድናት አካል ሆነዋል።
በትናንትናው ዕለት የተካሔዱት የምድብ ማጠቃለያ ግጥሚያዎች የተጠናቀቁት ሞሮኮ ኮሎምቢያን 1 ለ ባዶ በመርታትና ጃፓንና ጀርመን 1 ለ 1 በመለያየት ነው።
ጀርመን ከዓለም ዋንጫ የተሰናበተችው ከምድቧ ሶስተኛ በመሆኗና ከእያንዳንዱ ቡድን ለጥሎ ማለፍ የሚያልፉ ቡድናት ሁለት ብቻ በመሆናቸው ነው።
ኮሎምቢያ በሞሮኮ ብትረታም ቀደም ሲል ባስቆጠረቻቸው ግቦችና ባገኘቻቸው ከፍተኛ ነጥቦች ከምድቧ አንደኛ ሆና ለማለፍ በቅታለች።
ሞሮኮ ከተመሳሳይ ምድብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ወደ ጥሎ ማለፉ ተሸጋግራለች።
በዓለም ዋንጫ ውድድሩ ከተካፈሉት የአፍሪካ ቡድናት ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ለጥሎ ማለፉ ሲደርሱ ዛምቢያ ከምድቧ በሶስተኛ ደረጃ ጨርሳ ከውድድር ውጪ ሆናለች።
በጥሎ ማለፉ ውድድር እሑድ እኩለ ቀን ላይ ደቡብ አፍሪካ ከኔዘርላንድስ፣ ሰኞ አመሻሽ ላይ ናይጄሪያ ከእንግሊዝ፣ አውስትራሊያ ከዴንማርክ፤ ማክሰኞ ምሽት ሞሮኮ ከፈረንሳይ ይጋጠማሉ።
በውድድሩ ተሸናፊ የሆነ ቡድን ከዓለም ዋንጫ ተሰናባች ይሆናል።