የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን ለፊፋ ዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ካለፉት 16 ቡድናት ውስጥ በኔዘርላንድስ 3 ለ 1 በመረታት ከዓለም ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያው ተሰናባች ቡድን ሆኗል።
ለኔዘርላንድስ ግቦቹን ያስቆጠሩት ሜምፊስ ዲፔይ 10' ዴሊ ብላይንድ 45+1' እና ዴንዚል ዳምፍራይስ 81' ሲሆኑ፤ ሐጂ ራይት በ76ኛው ደቂቃ ለዩናይትድ ስቴትስ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
ኔዘርላንድስ በቀጣይነት ከአውስትራሊያና አርጀንቲና አሸናፊ ከሆነው ቡድን ጋር ቅዳሜ ዲሴምበር 10 ማለዳ 6፡00 am ለሩብ ፍፃሜ ውድድር ይጋጠማል።
አውስትራሊያ ውስጥ በየክፍለ አገራቱ ከትላልቅ የቲሌቪዥን ስክሪን የእግር ኳስ ደጋፊዎች ግጥሚያውን በቀጥታ እየተከታተሉ ነው።
የሜልበርን ፌዴሬሽን አደባባይ ለአውስትራሊያ ደጋፊዎች መመልከቻ ስለማይበቃ ተጨማሪ መመልከቻ ሥፍራ AAMI ፓርክ ላይ ተሰናድቶ በርካቶች ታድመው እየተመለከቱ ነው።
የአውስትራሊያና አርጀንቲና ጥሎ ማለፍ ግጥሚያ በመካሔድ ላይ ሲሆን፤ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ አርጀንቲና በሊዮኔል ሚሲ አማካይነት በ35ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ አውስትራሊያን 1 ለ 0 እየመራች ነው።


