በኢትዮጵያ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት በስፋት ጥቅም ላይ ከዋለ የአገር ዉስጥ እድገት (ጂዲፒ) 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጨምር ዓለም አቀፍ የሞባይል ግንኙነት ሥርዓት ማኅበር አስታወቀ።
ይህም የሚሆነው በፈረንጆች 2030 ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ 60 በመቶ ያህሉ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ ከሆኑ ነው ያለው ማኅበሩ፤ በተጨማሪም 700 ሺሕ ሰዎችን ከአስከፊ ድህነት እንደሚያወጣና የታክስ ገቢን በ300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጨምር አመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በአንፃራዊነት 99 በመቶ የኔትዎርክ ሽፋን ተደራሽነት ቢኖርም፤ የኔትዎርክ ጥራት አስተማማኝ አለመሆን፣ የዲጂታል ስርዓቱ ግንዛቤ ጉድለት፣ የዕምነትና የመረጃ ግላዊነትና ደህንነት ጥያቄ እንዲሁም የግብይቶች በተደጋጋሚ መስተጓጎል የሞባይል ገንዘብ ክፍያን እና አጠቃቀም ላይ እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም፤ በ2021 የኤሌክትሪክ ኃይል ያላቸው ኢትዮጵያውያን 51 በመቶው ብቻ በመሆናቸው ኤሌክትሪክም ሃይል አለመኖር ትልቅ ፈተና ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ጎረቤቶቿ ጋር ሲነጻጸር የገንዘብ ክፍያ ሥርዓት ተሳትፎዋ በጣም ዝቅተኛ ነው የተባለ ሲሆን፤ በ2022 በኬኒያ ከ80 በመቶ በላይ፣ በሩዋንዳ 77 በመቶ፣ በኡጋንዳ 66 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች የባንክ ወይም የሞባይል ገንዘብ መክፈያ አካውንት እንዳላቸው የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።
የወለድ መጠን
የአውስትራሊያ ብሔራዊ ባንክ የወለድ መጠን ባለበት 4.10 ፐርሰንት ላይ ረግቶ እንዲቆይ ወሰነ።
ማዕከላዊ ባንኩ ካለፈው ወር ሜይ አንስቶ ያካሔዳቸው 12 የወለድ መጠን ጭማሪዎች "በምጣኔ ሃብቱ የአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ሚዛን ይበልጡን ዘለቄታ እንዲኖረው" አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ያረካው መሆኑን አመልክቷል።
የባንኩ ቦርድ የወለድ መጠን ጭማሪን በእዚህ ወር የመግታት ውሳኔ የምጣኔ ሃብቱን ለመገምገም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚሰጠው ጠቅሷል።
በማከልም፤ የአውስትራሊያ ዋጋ ግሽበት ለተወሰኑ ጊዜያት ከፍ ብሎ እንደሚቆይ ጠቁሟል።
ወርሃዊ የሸማቾች ዋጋ ሰንጠረዥ በወርሃ ሜይ ከ 6.8 ፐርሰንት ወደ 5.6 ፐርሰንት ዝቅ ብሏል።