ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፣ በበዓሉ ላይ አላስፈላጊ ኃይል የተጠቀሙ እና ከመጠን ያለፈ እርምጃ ወሰዱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎ፣ በሕግ ተጠያቂ ከመሆናቸው በተጨማሪ በሕግ አስከባሪዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስፈላጊ ሥልጠና ማግኘት አለባቸው ብሏል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) በበዓሉ ላይ የተከሰቱትን ክስተቶች አስመልክተው በሰጡት ሀሳብ፣ የጸጥታ ኃይሎች በዓሉን ለማክበር በወጣው ሕዝብ ላይ ከልክ ያለፈ አላስፈላጊ ድብደባ፣ አስለቃሽ ጭስ፣ ጥይትና ሌሎች ከመጠን ያለፉ እምጃዎችን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተወሰደው እርምጃ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና ህጻናት ሳይቀሩ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ቢንስ አንድ ሰው መገደሉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሊም ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡ በምኒልክ አደባባይ የዓድን ድል ለማክበር፣ እንዲሁም በአቅራቢያው በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ሕዝባዊ በኃይል መበተኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
የሕዝብን ደህንነት ማስጠበቅ እና የኹሉንም ሰው ሰብአዊ መብቶች ማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነቱ የሆነው፣ የጸጥታ ኃይል የሚወስዳቸው አላስፈላጊ እና ከመጠን ያለፉ እርምጃዎች በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡