ከሜይ 21 አገራዊው ምርጫ በኋላ የተመራጩ የአውስትራሊያ ፈዴራል መንግሥት በጅሮንድ ለመሆን የሚሹት የሊብራሉ ጆሽ ፍራይደንበርግ እና የሌበሩ ጂም ቻልመርስ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ በካንብራ ብሔራዊ ፕሬስ ክለብ ተገኝተው የምርጫ ዘመቻ ክርክር አካሂደዋል።
ፍራይደንበርግና ቻልመርስ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት እያንዳንዳቸው የስድስት ደቂቃዎች የመክፈቻ ንግግር በማድረግ የፓርቲያቸውን የወደፊት የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ አቅጣጫዎች አመላክተዋል።
የሁለቱ ፓርቲ ተወካዮች ክርክር የተካሔደው የአውስትራሊያ የዋጋ ግሽበት ወደ 5.1 ካሻቀበና የብሔራዊ ባንክ የወለድን መጠንን ከ11 ዓመታት በኋላ በ 0.35 ፐርሰንት ከፍ ባደረገበት ማግስት ነው።
የመጀመሪያ ተናጋሪ የሆኑት ጂም ቻልመርስ ለፕሬስ ክለብ ታዳሚዎች የሌበር ፓርቲ የኑሮ ውድነትን ጫናን ለቤተሰቦች ያቀልላል፣ የደመወዝ ዕድገት እንዲኖር ያደርጋል፣ ምጣኔ ሃብቱ ያለ ተጨማሪ የዋጋ ግሽበት እንዲያድግ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "እኛ አቅርበን ያለነው ትርጉም ያለው ለውጥ እንጂ ስር ነቀል ለውጥን አይደለም። ከአንድ አሠርት ዓመታት በላይ ያህል የደረሰውን ጉዳት በአንድ በጀት፤ ሲልም በአንድ የመንግሥት የሥራ ዘመን የምናቃናው እንዳልሆነ እናውቃለን። አውስትራሊያውያን አሁን ካለው የተሻለ እንዲሆንላቸው እየጠየቁ ነው። መንግሥት በበኩሉ አሁን ያለውን ዓይነት ተመሳሳይ ሁነት እንደሚደግም ቃል እየገባላቸው ነው። ተመሳሳይ መንግሥት ማለት የኑሮ ውድነትና የደመወዝ ዕድገት ቁልቁል መውረድ የተጣመሩበት ቅጣት ማለት ነው" ብለዋል።
ጆሽ ፍራይደንበርግ በበኩላቸው፤ መንግሥታቸው የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁከት ያወጣና ለወደፊቱም ብርቱ ዕቅድ ያለው ስለመሆኑ አንስተዋል።
አያይዘውም "ምርጫው ይህ ነው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የሚመራውና በጀትን በጅቶ ከሚያውቀው ቅንጅት እና ከቶውንም በጀት በጅተው፣ የበጀሮድነት ሥፍራን ይዘው በማያውቁት፣ የወለድ መጠንንና የሥራ አጥነት ቁጥርን በማይለዩት አንቶኒ አልባኒዚ ነው። ይህ ለ26 ሚሊየን አውስትራሊያውያን ግልጹ ምርጫ" ሲሉ ተናግረዋል።