አርጀንቲናዊው ኮከብ የእግርኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ ወደ ፓሪስ ቅዱስ ጀርማይን ክለብ ለልምምድ ሲመለስ የክብር አቀባበል ተደረገለት።
ሜሲ አገሩን አርጀንቲናን ወክሎ ኳታር ላይ የፊፋ ዓለም ዋንጫን አሸንፎ ከተመለሰ ወዲህ ዕረፍት ላይ ነበር።
ለሰባት ጊዜያት በዓለም ኮከብ ተጫዋችነት የተሰየመው ሜሲ ለክለቡ ዳግም ለመጫወት ዝግጁነቱን አስታውቋል።
አውስትራሊያ - ቻይና
ባለፈው ዓመት ማብቂያ ወርሃ ዲሴምበር ላይ በአውስትራሊያና ቻይና መካከል መልካም መግባባትን ያሳየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ተከትሎ ቻይና ዕቀባዋን ወደ ጎን በማለት የአውስትራሊያን ደንጊያ ከሰል መግዛት ልትቀጥል ነው።
ቻይና ከ2020 ወዲህ ደንጊያ ከሰልን ጨምሮ በርካታ የአውስትራሊያ ምርቶች ላይ ይፋ ያልሆነ ማዕቀቦችን ጥላ ቆይታለች።
የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ከአውሮፓውያኑ ገና በፊት ከቻይናው አቻቸው ዋንግ ዪ ጋር ቤጂንግ ላይ ያካሔዱትን ስብሳባ "በጣሙን ገንቢ" ሲሉ ገልጠውታል።