የትግራይ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ትናንት ጥቅምት 25 ከመቀሌ ባወጣው መግለጫ የሰላም ንግግሩ ስምምነት የትግራይን ሕዝብ ፍላጎቶች ማዕከል በማድረግ የሚተገበር መሆኑን ገለጠ።
መግለጫው ሕወሓትን በስም ሳይጠቅስ "የትግራይ መንግሥት" በማለት የተጠቀመ ሲሆን፤ "ውድመትን በመግታት ለሕዝባችን ምቹ ሰላማዊ ሕይወትን ለመፍጠር ሕዝብና የትግራይ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ማቅረባቸው የሚታወቅ ነው" ብሏል።
በማከልም፤ የደቡብ አፍሪካውን የሰላም ንግግር ከግጭት መገታት ስምምነት ጠቅሶ ሁነኛ ያላቸውን ግቦች ሲያመላክት " የወራሪዎች ከትግራይ መውጣትና ገደብ አልባ ሰብዓዊ ረድኤቶች ወደ ትግራይ እንዲዘልቁ" መሆኑን ጠቅሷል።
ቢሮው የስምምነቱ ዋነኛ ስኬት "የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከበሬታ" እንደሆነም አመላክቷል።
አክሎም፤ የስምምነቱን ዝርዝር በተመለከተ 'የትግራይ መንግሥት' ማብራሪያዎችን በተከታታይ እንደሚሰጥ ጠቁሞ፤ የትግራይን ሕዝብ ሕልውና የሚጎዳ ስምምነትንም ሆነ ተግባርን እንደማይቀበልም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት በተመራው የደቡብ አፍሪካ የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ ቡድን መሪ ሆነው በመገኘት ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ትናንት ጥቅምት 25 ለከፍተኛ የመንግሥት አመራር አባላት ገለጣ አድርገዋል።
በአምባሳደሩ የሰላም ስምምነት ገለጣ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አክሎ የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን የገለጣቸውን ዋነኛ ጭብጮች አስመልክተው ለአገር ውስጥ ብዙኅን መገናኛ ባስረዱበት ወቅት፤ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መከበርን ማረጋገጥና ሉዓላዊነትን በማስከበር በኩል ከመተማመን ላይ እንደተደረሰ፣ የሽግግር ጊዜ ሂደትን፣ የወደሙትን መጠገንን፣ የደረሱ ጥፋቶችን መልሶ መመልከትን፣ አንድነትንና በጋራ ተያይዞ መቀጠልን ያቀፈ ስለመሆኑ በአንኳርነት አንስተዋል።