የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች መሪ ኖል ፒርሰን የሊብራል ፓርቲ ለነባር ዜጎች ድምፅ ለፓርላማ እንዳይመሠረት የአውስትራሊያ ሕዝብ ላይ በፋሲካ ዋዜዋ "የይሁዳን ክሕደት" ፈፅሟል ሲሉ የከረረ ትችት ሰነዘሩ።
አቶ ፒርሰን የነባር ዜጎች ድምፅ ለፓርላማ እንዲመሠረትና በሕገ መንግስቱም ውስጥ እንዲሠፍር ጥሪ ያቀረበው የኡሉሩ መግለጫ አርቃቂና አውጪ ከሆኑት መሪዎች አንዱ ናቸው።
እንዲህ ላለው ብርቱና በእጅጉ ጠቃሚ አገራዊ ጉዳይ ድጋፍን መንሳት በእጅጉ አሳዛኝ እንደሆነ አመላካተው፤ የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን ድምፅ ለፓርላማን ተፃርሮ መቆም "አገሪቱን ሃፍረት ያላብሳል" ሲሉ ለSBS ተናግረዋል።
አክለውም "እሱ [ፒተር ዳተን] ኡሉሩን ለመቅብር ይሞክራል፤ ይሁንና ይሳካላታል ብዬ አላስብም። የዳተንና ፖሊን ሃንሰን የጋራ ቲኬት ለስኬት ይበቃል ብዬ አላስብም። በምንም ዓይነት ለስኬት መብቃት የለበትም። አገሪቱ ለወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ከዚህ የተሻለ ይገባታል" ብለዋል።
በሌላም በኩል፤ የቀድሞው የሊብራል ፓርቲ ነባር ዜጎች ሚኒስትር የነበሩት ኬን ዋይት በአቶ ዳተን ድምፅ ለፓርላማ ተፃራሪ አቋም ሳቢያ የሊብራል ፓርቲ አባልነታቸውን ሰርዘዋል።
አቶ ዳተን ድምፅ ለፓርላማን ተቃውመው የሕገ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ ዘመቻ እንደሚያካሂዱና ሆኖም ምልክታዊ የሆነ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ቢያገኙ የማይቃወሙ መሆናቸው ትናንት ይፋ አድረገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ በአንድነት ቆሞ ድጋፉን ለድምፅ ለፓርላማ እንዲቸር ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድምፅ ለፓርላማ ጥሪያቸውን ያቀረቡት የአውስትራሊያ ሙስሊም ወዳጅነት ባዘጋጀው ብሔራዊ ኢፍጣር የእራት ግብዣ ላይ ተገኝተው ነው።
የአቦርጂናልና ቶረስ መሽመጥ ደሴተኞች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናን ማላበስ ለአውስትራሊያ ሕብረትና አንድነትን ማጎናፀፊያ ወቅት እንደሆነ አስገንዝበዋል።