በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የተከሰተው ክስተት አየተባባሰና እየተካረረ መሄዱ በእጅጉ እንዳሳሰበው ተቋሙ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዛሬው ዕለት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
የስድስቱ አባል የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ስለጉዳዩ በመጨነቅ አብዝተው ከመጸለይ ባለፈ ከቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር ችግሩ በሰላማዊ ሁኔታ ስለሚፈታበት ሁኔታ መወያየታቸውም ተገልጿል።
በተያያዘም በዚህ ሂደት ተቋሙ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
ቤተክርስቲያኒቱ ለዘመናት የኖረ ሕገ ቤተክርስቲያን፣ ቀኖና እና ሥርዓት ያላት አንጋፋ ተቋም ከመሆኗ አንጻር ያጋጠማትን ውስጣዊ ችግር በቤተክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት ሊፈታ እንደሚችል እንጠብቃለን በማለት ገልጿል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ ባለ አምስት ነጥብ መግለጫም አውጥቷል።
ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አማኞች በተጨማሪ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ፊቱን ወደ ፈጣሪ በመመለስ ጸሎት ወይም ዱዓ እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።
የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ከማክበር ጎን ለጎን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ተገንዝበው ውይይትን፣ ይቅርታንና እርምትን እንዲያስቀድሙ በፈጣሪ ስም በማሳሰብ ይህም ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድማችሁ እንድትከላከሉ ሲል ገልጿል።
የፌዴራልና የክልሎች መንግሥታት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠረው ችግር በራሷ በቤተክርስቲያኒቱ ሕግ፣ ቀኖና እና ሥርዓት ብቻ ተመሥርቶ እንዲፈታ ኃላፊነታቻውን በአግባቡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 እና አንቀጽ 27 መሠረት እንዲወጡ ተቋሙ አሳስቧል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አመራሮችና አባላት፤ የማኅበረሰብ አንቂዎች ወቅታዊ የቤተክርስቲያኒቱን ውስጣዊ ችግር ከማባባስ እንዲጠበቁ ተቋሙ አደራ ብሏል።
የመገናኛ ብዙኋን ባለሙያዎች፣ ዘጋቢዎችና ተንታኞች የሚያስተላልፏቸው መልእክቶችና ንግግሮች ችግርን የሚያባብሱና ሌላ ግጭትና ሁከት የሚቀሰቅሱ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል።