የረድዔት አቅርቦት የያዙ 27 የጭነት መኪናዎች 1,000 ሜትሪክ ቶን ያህል ምግብና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ይዘው መቀሌ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መዝለቃቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ትናንት ሐሙስ ኒውዮርክ ላይ ገለጡ።
ይኼው የረድዔት አቅርቦት የእርዳታ ማጓጓዙ ከቀጠለበት ወርሃ ኤፕሪል ወዲህ አራተኛው መሆኑንና በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም በ169 የጭነት ተሽከርካሪዎች 4,300 ሜትሪክ ቶን ትግራይ መድረሱን ጠቅሰዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ረድዔቶች ከመዲናይቱ መቀሌ የእርዳታ ቅድሚያ ወደሚያሻባቸው የተለያዩ አካባቢዎች መሰራጨቱን አመላክተዋል።
ለስርጭቱ ተደራሽነትም በቅርቡ የደረሰው የነዳጅ አቅርቦት ሁነኛ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
በማያያዝም ወደ ትግራይ እየዘለቁ ያሉት አቅርቦቶች ከአስፈላጊው መጠን አኳያ ሲነፃፀር አንስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተመድና ሽርካዎቹ በጋራ በመሆን ዘርና ማዳበሪያን አካትቶ የረድዔት አቅርቦቶችን መጠን ከፍ በማድረግ ከባለስልጣናቱ ጋር በመተባበር እየሠሩ መሆኑም ተገልጧል።
አቶ ዱጃሪች ተመድ ከባለስልጣናት ጋር ተባብሮ በመሥራት በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን የግጭት ተጎጂ ለሆኑት የአፋርና አማራ ክፍለ አገራት አስፍቶ እያዳረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ባለፈው ሳምንትም ምግብ ለጋሽ የተመድ ሽርካዎች አማራ ክፍለ አገር ውስጥ ለ 56,000 ያህል ሰዎች ረድዔት መለገሳቸው ተነግሯል።
ካለፈው ወርሃ ዲሴምበር አንስቶም ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከመንግሥት፣ ከተመድና የረድዔት ድርጅቶች የምግብ እርዳታ ማግኘታቸው ተጠቅሷል።