በጋና መዲና አክራ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ፕሬዚደንት ናና አኩፎ አዶ ከስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ።
በቁጣ የተመሉት የተቃውሞ ሰልፈኞች ፕሬዚደንቱ ከስልጣን እንዲለቅቁ ድምፃቸውን ያሰሙት ለጋና ከሬኮር ያለፈ የነዳጅና ምግብ ዋጋ ማሻቀብ ተጠያቂው ፕሬዚደንቱ ናቸው በሚል ዕሳቤ ነው።
ቀይ ካናቴራ ያጠለቁት ተቃዋሚ ሰልፈኞች አክራ አደባባይ ላይ ይዘዋቸው ከወጡት መፈክሮች ውስጥ "አኩፎ አዶ የግድ መሰናበት አለባቸው" እና የጋናውን ፕሬዚደንት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር እያካሔዱ ያለውን ድርድር በማመላከትም "እምቢኝ ለዓለም ገንዘብ ድርጅት" የሚሉ መፈክሮች ይገኙባቸዋል።
የጋና ገንዘብ ከሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር ምንዛሪው በ40 ፐርሰንት ያሽቆለቆለ ነው።
በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ሩብ ያህል ጋናውያን የሚኖሩት በቀን 2.15 የአሜሪካ ዶላር ባነሰ ገቢ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ
አውስትራሊያ የተባበሩት መንግሥታትን የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ በ2026 ለማዘጋጀት ፈቃደኛ መሆኗን አስታወቀች።
የአውስትራሊያን የ2026 የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ የማስተናገድ ፈቃደኝነት ዛሬ ማለዳ ላይ የገለጡት የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ክሪስ ባወን ናቸው።
ሚኒስትሩ የአውስትራሊያ መንግሥት ካቢኔ በ2026 አውስትራሊያ የCOP31 አስተናጋጅ አገር ለመሆን ፈቃዱ መሆኑን በስምምነት ያረጋገጠላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የ2024 የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ለምሥራቅ አውሮ ፓ አገር የተሰጠ ሲሆን የ2026 ኮንፈረንስ ለምዕራብ አውሮፓና ሌሎች ፈቃደኛ አገራት በታሳቢነት የተያዘ ነው።