የፊታችን ማክሰኞ ሜይ 9 ይፋ በሚሆነው 2023/2024 ዓመታዊ በጀት የፌዴራል መንግሥቱ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ድጎማዎችን ለማድረግ መወጠኑን በጅሮንድ ጂም ቻልመርስ ጠቆሙ።
የብጅሮንዱን ቅድመ በጀት ፍንጭ ተመርኩዞ 5.5 ሚሊየን አውስትራሊያውያንና 1.1 ሚሊየን አነስተኛ ንግዶች ለኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ መደጎሚያ የሚውል እስከ $500 ድረስ ሊያገኙ እንደሚችል ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነገሩ ነው።
ይሁንና በጅሮንዱ 'በርካታ ዶላሮች' እና 'እንደ ክፍለ አገራቱ የኤሌክትሪክ ዋጋ መጠን' ከማለት በስተቀር ትክክለኛውን የድጎማ ቁጥር አልተናገሩም።
በታካይነትም ለሥራ አጥነት የድጎማ ክፍያም ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል በመነገር ላይ ይገኛል።
በሌላም በኩል አውስትራሊያ ከ15 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቢሊየን ዶላሮች የሚቆጠር ተረፈ ፈሰስ ስለማግኘቷ በማክሰኞው የበጅሮንድ ቻልመርስ የበጀት ሪፖርት ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የሴቶች ዓለም ዋንጫ 2023
ዓለም ዓቀፍ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር (ፊፋ) ዘንድሮ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ በጥምር የሚካሔደውን የሴቶች የዓለም ዋንጫ "ለአምስት ትላልቅ" የአውሮፓ አገራት የስርጭት ፈቃድ ሊከለክል እንደሚችል አስጠነቀቀ።
ለፊፋ ማስጠንቀቂያ አስባብ የሆነው አምስቱ አገራት ለሴቶች የእግር ኳስ ዋንጫ ስርጭት ፈቃድ መብት ያቀረቡት የገንዘብ መጠን ከወንዶች የዓለም ዋንጫ ውድድር የቀጥታ ስርጭት ፈቃድ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ነው።
አምስቱ "ትላልቅ" ተብለው የተጠቀሱት የአውሮፓ አገራት እንግሊዝ፣ ስፔይን፣ ጣሊያን፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ናቸው።
አምስቱ አገራት ቀደም ሲል ለወንዶች የዓለም ዋንጫ የቀጥታ ስርጭት መብት ከ$100 ሚሊየን እስከ $200 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለመክፈል ፈቃደኞች መሆናቸውንና ለዘንድሮው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ግና መክፈል የፈለጉት ከ$1.5 ሚሊየን እስከ $15 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብቻ መሆኑን የፊፋ ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ይፋ አድርጓል።
ፕሬዚደንቱ ይህንኑ የአውሮፓ አገራት የቀጥታ ስርጭት መብት ግዢ እሳቤ የመላው ዓለም ሴቶችን "ፊት በጥፊ እንደማጮል ነው" ሲሉ አክርረው ተችተዋል።
አያይዘውም "በጣሙን ግልፅ ለመሆን፤ የፊፋ የሴቶች ዓለም ዋንጫ ውድድርን አሳንሶ አለመሸጥ የእኛ የሞራልም ሕጋዊም ግዴታ ነው" ብለዋል።
የ2023 የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ውድድር የመክፈቻ ሥነ ሥርዓትና ግጥሚያ ጁላይ 20 በኒውዝላንድ ኤዳን ፓርክ ኦክላንድ ከተማ ይጀመራል።