የዲሞክራቱ ዕጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በፕሬዚደንት ትራምፕ ላይ ያላቸው አብላጫ ድምፅ እየጨመረ መምጣትን ተከትለው 46ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት እንደሚሆኑ ያላቸን ሙሉ ተስፋ ገልጠዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ለመሆን 270 የምርጫ ኮሌጅ ድምፆችን ማሸነፍ ግድ ይላል። አቶ ባይደን በአሁኑ ወቅት በፎክስ ኒውስ ስሌት 264 የምርጫ ድምፆችን ያሸነፉ ሲሆን በCNN ስሌት 253 ድምፆችን አግኝተዋል።
ይሁንና ከሚያሻቸው የምርጫ ኮሌጅ ድምፆች በላይ የሚያስገኙላቸውን ፔንሲልቫኒያ (20)፣ አሪዞና (11)፣ ጂርጂያ (16) እና ኔቫዳ (6) እየመሩ ይገኛሉ። አቶ ባይደን የፔንሲልቫኒያን 20 የምርጫ ኮሌጅ ድምፅ ብቻ ካሸነፉ ቀጣዩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ለመሆን ከሚያሻቸው 270 ድምፆች በላይ የሚያስገኝላቸው ሲሆን በእሳቸው ግምት ከ300 በላይ የምርጫ ኮሌጅ ድምፆችን እንደሚያሸንፉ ያላቸውን እምነት ገልጠዋል።
ከጠቅላላ የመራጮች ድምፅ ውስጥም አቶ ባይደን እስካሁን ከ74 ሚሊየን በላይ ሲያሸንፉ አቶ ትራምፕ ከ70 ሚሊየን በላይ በላይ ድምፆችን በማግኘት እየተከተሉ ይገኛሉ።
አቶ ትራምፕ ግና ምንም እንኳ ይህ ነው የሚባል ማስረጃ ባያቀርቡም በምርጫ ሂደቱ የተጭበረበሩ ድምፆች አሉ በማለት ቁልፍ በሆኑ ስቴቶች የድምፅ ቆጠራው እንዲቆም ወይም ዳግም ቆጠራ እንዲደረግ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩ አስታውቀዋል።
ይህንንም በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ማንም ይመረጥ ማን ቀደም ሲል ከነበሩት ፕሬዚደንት ጋር አብረው እንደሠሩ ሁሉ ከቀጣዩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጋርም በጋራ እንደሚሰሩ ገልጠዋል።
ቫይረስ ቪክቶሪያ
ቪክቶሪያ እስከ ዛሬ ቅዳሜ ኖቬበር 7 ላለፉት ስምንት ቀናት በኮረናቫይረስ የተያዘም ሆነ ሕይወቱ ያለፈ ግለሰብ ሳታስመዘግብ ቆይታለች።
በነገው ዕለት እሑድ ኖቬበር 8 እስካሁን ተጥለው ያሉት የኮሮናቫይረስ ገደቦችን መርገብ አስመክቶ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ መግለጫ ይሰጣሉ።
የቪክቶሪያ ጤና ሚኒስትር ማርቲን ፎሊ ቪክቶሪያ እየካሄደች ያለችው የወረርሽኝ መከላከል ዘለቄታ እንዲኖረው ማስቀጠል ግድ እንደሚሆን አሳስበዋል።