የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሕዳር 28 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሱ ያሉ መጠነ ሰፊ ግድያዎች፣ የአካል ማጉደላና መፈናቀሎች አስመልክቶ የፌዴራል መንግሥቱ አፋጣኝና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ኮሚሽኑ ቀደም ሲል ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት፣ "በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ እንደወደቀ መቀጠሉንና በተለይም በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ኃይሎች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሲቪል ሰዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል፣ ለዘረፋ እና ለንብረት ውድመት መዳረጋቸውን" በ12 ወራት ሪፖርቱ ላይ ማስፈሩን አውስቷል።
አክሎም፤ የኮሚሽኑ ሰብዓዊ መብቶች ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገበት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና የሚደርሱ ጥቃቶችን፣ በእነዚህም ሳቢያ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መከታተሉንም ጠቅሷል።
ይህንኑ መግለጫ ይፋ እስካደረገበት ዕለትም ጊዜ ድረስ በኮሚሽኑ ክትትል ከዚህ ቀደም ግጭት የተከሰተባቸው ወይም እየተከሰተባቸው ያሉ ተብለው የተመዘገቡ አካባቢዎች በስም ጠሱ አስፍሯል።
- በምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ፣ መነ ሲቡ ወረዳ (ነጆ መንዲ ከተማ)፣ ለታ ሲቡ፣ ቦጂ ድርመጂ (ቢላ ከተማ)፣ ነጆ ከተማ፣ ቆንዳላ ወረዳ፣ ቤጊ ወረዳ፣ ቅልጡ ካራ ወረዳ፤
- በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ ዴጋ ወረዳ፣ ሳሲጋ ወረዳ፣ ጊዳ አያና ወረዳ፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ጉትን ወረዳ፣ ሊሙ ወረዳ፣ ጅማ አርጆ፤
- በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ (አሊቦ፣ ጃርደጋ እና ጃርቴ ከተሞች)፣ አሙሩ ወረዳ (አሙሩ ከተማ፣ አገምሳ ከተማ እና ከ10 በላይ ቀበሌዎች)፣ ሆሮ ቡልቅ ወረዳ፣ ጉዱሩ ወረዳ፤
- በቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ ሀዋ ገላን ወረዳ (መንደር 20 እና 21)፤
- በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ሜታ ወልቂጤ ወረዳ፣ አደዓ በርጋ ወረዳ፣ ጮቢ ወረዳ፣ ጀልዱ ወረዳ፣ አቡና ግንደበረት ወረዳ፣ ግንደበረት ወረዳ፣
- በምሥራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ ቦሰት ወረዳ፣ ዱግዳ ወረዳ፣ ፈንታሌ ወረዳ፤
- በአርሲ ዞን ውስጥ ጀጁ ወረዳ፣ መርቲ ወረዳ፤
- በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ኩዩ ወረዳ ወረጃርሶ ወረዳ፣ ደራ ወረዳ፤
- በኢሉ አባ ቦር ዞን ውስጥ ደርሙ ወረዳ፣ አሊጌ ሰቺ ወረዳ፤
- በቡኖ በደሌ ዞን ውስጥ ጨዋቃ ወረዳ፣ ዳቦ ሃና ወረዳ፣ መኮ ወረዳ፣ ዴጋ ወረዳን ያጠቃልላሉ።
በተያያዥነትም፤ በተለያዩ ወቅቶች በእነዚህ በተዘረዘሩት አካባቢዎች በታጣቂነት የሚንቀስቅሱ ኃይላትን ሲጠቅስም "የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም በመንግሥት እራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚል የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሌሎች ክልሎች ጭምር እንደመጡና በተለምዶ በአካባቢው የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸውን የሚነገሩ የታጠቁ ቡድኖች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) እንደሚንቀሳቀሱ ታውቋል" ብሏል።
ኮሚሽኑ በማከልም "በግጭት አውድ ውስጥ እና በግጭቶቹ ሳቢያ ከሚደርሱ ግድያዎች፣ መፈናቀል፣ አካል ጉዳት፣ ዘረፋዎች፣ የአካባቢ ውድመቶችና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ በአንድ በኩል ታጣቂዎቹ ወይም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አካባቢዎቹን በተቆጣጠሩበት ወቅት፣ በሌላ በኩል ግጭት ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችም በእኩል ደረጃ ሊያሳስቡ የሚገባ ነው" ሲል አሳስቧል።