የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ተጫዋቹ ኖቫክ ጆኮቪች ለ10ኛ ጊዜ የአውስትራሊያን ኦፕን ዋንጫ ለማንሳት ዛሬ ወደ ሜልበርን አቅንቷል።
ጆኮቪች ትናንት እሑድ ታህሳስ 30 አሜሪካዊ ተቀናቃኙን ሰባስቲያን ኮርዳን በአደላይድ ዓለም አቀፍ ግጥሚያ በሶስት ዙር ግጥሚያ ረትቷል።
የአደላይዱ ግጥሚያ ጆኮቪች በኮቪድ-19 ክትባት አለመከተብ ሳቢያ ባለፈው ዓመት አውስትራሊያን ለቅቆ እንዲወጣ ከተደረገ ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
ለግጥሚያ ወደ አውስትራሊያ ከመመለሱ ጋር ተያይዞ ደጋፊዎቹ የሞቀ አቀባበል አድርገውለታል።
ጆኮቪቺም የአፀፋ ምስጋና ምላሹን አቅርቧል።
ሩስያ ዩክሬይን
የዩክሬይን መከላከያ ሩስያ በሰነዘረችው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩክሬይን ወታደሮችን ገደልኩ ያለችው "ፕሮፖጋንዳ" ነው ሲል አስተባበለ።
ሩሲያ በፊናዋ በምሥራቃዊቷ ክራማቶርስክ ከተማ በወነጨፈችው የሚሳይል ጥቃት ከ600 በላይ የዩክሬይን ወታደሮችን ሕይወት መንጠቋን አስታውቃለች።
የዩክሬን ወታደራዊ ዕዝ የሩስያን መግለጫ ሐሰት ሲል፤ የክራማቶርስክ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የሩስያ ሚሳይል የተወሰኑ የንብረት ውድመት እንዳደረሰ ገልጠው የሕይወት ጥፋት ስለማድረሱ ግና የተመለከቱት ማስረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።