ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ከአውስትራሊያ የንግድ ልዑካንና የዩኒቨርሲቲ መሪዎች ጋር ሆነው ሕንድ ገቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕንድ እንደደረሱ በሕንዱ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
አቶ አልባኒዚ በጉጃራት ተገኝተው ሳባርማቲ አሽራምና የነፃነት ተፋላሚውን ማሃታማ ጋንዲን መታሰቢያ ጎብኝተዋል።
የአውስትራሊያ ልዑካን ቡድን ለሶስት ቀናት በሕንድ አህመዳባድ ከተማ የሚቆዩ ሲሆን፤ ትኩረታቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማጠናከር ላይ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚን የሕንድ ጉዞ ተከትሎ በተለይም በሕንድ ሙስሊሞች ላይ የደረሱት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ትኩረት የሚያገኙ ይሆናሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ የሂንዱ ብሔረተኛነት የከረረ መሆኑን የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና የፖለቲካ ተጠባቢዎች እያመላከቱ ነው።

Credit: Indian census, 2011
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልቴንበርግ ሩስያ የምሥራቃዊ ዩክሬይን ከተማ ባክህሙትን በቅርቡ ልትቆጣጠር እንደምትችል ተናገሩ።
ዋና ፀሐፊው ትንበያቸውን የሰነዘሩት የአውሮፓ መከላከያ ሚኒስትሮች ስዊድንና ፊንላንድን ለድርጅቱ ለማስተዋወቅ በታደሙበት ስብሰባ ላይ ነው።
አቶ ስቶልቴንበርግ በዩክሬይን በኩል የሚቻለውን ያህል የመቋቋም ጥረት ቢደረግም ሩስያውያኑ ከተማይቱን ለመቆጣጠር ብርቱ እመርታ እያደረጉ መሆኑን በአፅንዖት ገልጠዋል።