ትናንት እሑድ ሜይ 8 / ሚያዝያ 30 ምሽት በቻናል 9 ቴሌቪዥን በጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንና የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዚ መካከል ለሁለተኛ ጊዜ አገራዊ ምርጫውን ተከትሎ ክርክር ተካሂዷል።
በክርክሩ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የቻይና ወታደራዊ ጦር ሠፈር የማግኘት ሁኔታ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ደኅንነትን የሚፃረር መሆኑን አሳስበዋል።
አቶ ሞሪሰን ቀደም ባሉ ሳምንታት በምርጫ ዘመቻቸው ላይ የቻይናን በሰለሞን ደሴት የጦር ሠፈር ማግኘት አስመልክተው "ቀይ መስመር" ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሁ እንዲያብራሩ በጋዜጠኞች ተጠይቀዋል።
አርኪ ምላሽም ባይሆን " ያ ማለት ከአውስትራሊያ ብሔራዊ ጥቅም፣ እንዲሁም ከሰለሞን ደሴቶች ጥቅም አኳያ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ሲሆን ነው" በማለት ተናግረዋል።
ይሁንና "ከወዲሁ ይህ ይሆናል ማለት ብልህነት አይደለም" ከማለት ባሻገር ቻይና ወታደራዊ ጦር ሠፈሯን ሰለሞን ደሴቶች ላይ ብትገነባ መንግሥታቸው ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አልገለጹም።
በክርክሩ ወቅት አቶ አልባኒዚና አቶ ሞሪሰን የደመወዝ ማስተካከያ መጠንን አስመልክተው ጋል ያለ ክርክር አድርገዋል።
አቶ አልባኒዚ የሌበር መንግሥት ከተመረጠ የደመወዝ ጭማሪ ከፍ እንዲል የሚያደርግ መሆኑን ደግመው በአፅንዖት አስታውቀዋል።
ሌበር በአቶ ሞሪሰን አስተዳደር ከደመወዝ በስተቀር ሁሉም ነገር መጨመሩን ደጋግሞ አክርሮ ይተቻል።
አቶ አልባኒዚ "በእኔና በወቅቱ መንግሥት መካከል ያለው ልዩነት፤ በእኛ በኩል እርምጃዎችና መዋቅሮች ዝቅተኛ ደመወዝን እንዲያሻሻሉ ማድረግ ነው" ብለዋል።
ክርክሩ እንዳበቃ ቻናል 9 ከ19 ሺህ አስተያየት ሰጪዎች አገኘሁ ባለው አስተያየት መሠረት 52% ስኮት ሞሪሰን አሸንፈዋል ሲሉ 42% ለአልባኒዚ ድጋፍ መቸራቸውን አስታውቋል።
ሆኖም ዳግም ከ30 ሺህ ሰዎች ተሰጠ በተባለው አስተያየት 51 ፐርሰንት አንቶኒ አልባኒዚን አሸናፊ ማለታቸውና ስኮት ሞሪሰን 49% ፐርሰንት የአስተያየት ሰጪዎችን ድጋፍ ማግኘታቸው ተገልጧል።
ትናንት እሑድ ማምሻውን ይፋ በሆነው ኢፕሶስፖል የሕዝብ አስተያየት ስብስብ መሠረት የሌበር ፓርቲ የአቶ ሞሪሰንን ጥምር ፓርቲ 52 ለ 40 እየመራ መሆኑ ተመልክቷል።
እንዲሁም፤ በኒውስፖል የሕዝብ አስተያየት ስብስብ መሠረት የሌበር ፓርቲ የአቶ ሞሪሰንን ጥምር ፓርቲ 54 ለ 46 እየመራ መሆኑ ተመልክቷል።
የሶስተኛው ዙር የመሪዎች ክርክር ረቡዕ ሜይ 11/ ግንቦት 3 በቻናል 7 ቴሌቪዥን አማካይነት ይካሔዳል።