የሌበር ፓርቲ ከ10,000 በላይ ለሚሆኑ ቤት ገዢ አውስትራሊያውያን እስከ 40 ፐርሰንት የሚደርስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የቤት ግዢ ድጎማው ለአዲስ ቤት ገዢዎች እስክ 40 ፐርሰንት ተገንብተው ለቆዩ ቤት ገዢዎች እስከ 30 ፐርሰንት ይሆናል።
ድጎማው ለአዲስ ቤት ገዢዎች እስከ $380,000 ተገንብተው ለቆዩ ቤቶች ገዢዎች $285,000 ያህል የሚያስገኝ ሲሆን፤ እንደ የክፍለ አገራቱ ከ$550,000 እስከ $950,000 የግዢ ጣራ ገደብ ተጥሎበታል።
አውስትራሊያውያን ከፌዴራል መንግሥቱ ቤታቸውን መግዛት የሚችሉ ሲሆን ለግዢ ለመብቃት የሁለት ፐርሰንት ቀብድ መክፈልና የመደበኛ ብድር መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
የኦንላይን ደኅንነት ጥበቃ
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን መንግሥታቸው ዳግም ከተመረጠ ልጆች፣ ሴቶችን፣ ቤተሰቦችንና ትምህርት ቤቶችን ያካተተ የኦንላይን ደኅንነት ጥበቃ ወጪን እንደሚሸፍን አስታወቁ።
በዚህም መሠረት $23 ሚሊየን የኢሴፍቲ ኮሚሽን በመላ አውስትራሊያ ላሉ መምህራን የስልጠና ፕሮግራሞችን እንዲያካሂድና የኦንላይን ደኅንነት ጥበቃ ማሻሻያ ይውላል።
እንዲሁም የኢሴፍቲ ኮሚሽን ከሕግ አስከባሪ ኤጄንሲዎች ጋር ትብብር በማካሔድ ግልጋሎቶችን መስጠት እንዲችል $10 ሚሊየን እንዲሁም፤ ለመድብለ ባሕል ማኅበረሰባት የኦንላይን ደኅንነት ጥበቃ ግልጋሎት ማጠናከሪያ $2 ሚሊየን ተመድቧል።
ሜይ 8 በጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንና የሌበር መሪ አንቶኒ አልባኒዚ መከክል በ9 ኔትዎርክ አጋፋሪነት ለሁለተኛ ጊዜ የምርጫ ክርክር ይደረጋል።
ግብፅ
በሰሜናዊ ሳይናይ ሰርጥ ባለ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ላይ ፍንዳታ መድረሱን የግብፅ ባለስልጣናት አስታወቁ።
የቢር አል አብድ ከተማ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለፍንዳታ የዳረጉት ፈንጂዎቹ የተጠመዱት በሚሊሺያዎች መሆኑም ተገልጧል።
በፍንዳታው ወቅት ግዙፍ የእሳት ነበልባል አየር ላይ መጓኑንና ሆኖም በሰው ሕይወት ላይ ጥፋትም ሆነ ጉዳት አለመድረሱን ባለ ስልጣናቱ ተናግረዋል።
እስካሁን ለፍናዳታው ኃላፊነቱን የወሰደ የለም።