የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ለሶስት ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነቀፌታና ምስጋናን አካትቷል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ የነነዌ ፆምና ምሕላ ልዩ በሆነ በመንፈሳዊ የንስሐ ጸሎት በሰላም መጠናቀቁን ገልጦ፤ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እስከ ምዕመናን የተካሔደው ምሕላና ፀሎት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ "የመጣው ፈተና እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ነው" ሲል አመላክቷል።
አያይዞም፤ በጾምና ንስሐው ወቅት ምእመናን የአባቶችን ጥሪ ሰምተው ሹመኞች ሳይፈሩ ፀሎትና ምሕላ ለአምላክ ማቅረባቸው ለእምነታቸው ፅኑ፣ ለአገር አንድነትና ሰላም ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የገለፁበትና ያም መንፈሳዊ ብርታትን ለአባቶች ያጎናፀፈ መሆኑን ገልጧል፡፡
በታካይነትም የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ "ጥቃቱ የቤተ ክርስቲያንን እውነት በካዱና በእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መካከል ነው፡፡ ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ሕግጋትን ጥሰው ሕገወጥ የጳጳሳት ሢመት በመደረጉ ነው" ሲል ጠቅሶ "በአፀፋው ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ይህን ጥሰት የፈፀሙትን ግለሰቦች አውግዛ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የለየቻቸው " መሆኑን አውስቷል።
ሆኖም "ጉዳዩ ከግለሰቦቹ በላይ በመንግሥት ስልጣን ላይ ባሉና ጽንፈኛ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር የሚደገፍ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል" ሲል አሳስቧል።
በሁነቱም፤ የቤተ ክርስቲያን ክብርና ተቋማዊ ልዕልና እንደተደፈረ፣ የቤተክርስቲያን ቅጥሮች መሣሪያ በያዙ አካላትና በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኃይልና በጉልበት እንደተወረረ፣ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት አህጉረ ስብከት ያለአንዳች የሕግ መሠረት በጸጥታ መዋቅሮች እንደተባረሩ፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቶቻቸው ተገድቦም በግዞት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ እንደተደረጉ፣ ወደ አህጉረ ስብከታቸውም ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ እቀባ እንደተደረገባቸው፣ ካህናት አባቶች እና ምእመናንም ያለአንዳች የሕግ መሠረት በየእስር ቤቱ ያለበቂ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ዘብጥያ ወርደው እንዳሉ፣በጸጥታ ኃይል ከመጠን በላይ ከመደብደባቸው የተነሳ የሞት፣ የከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት መሆኑንና በጥቅሉ በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈፀመባቸው አስታውቋል።
በተጨማሪም መግለጫው፤ ምእመናን ልጆቻቸው ጥቁር ለብሰው ወደ መሥሪያ ቤት እንዳይገቡ፣በመንግሥት ቢሮዎችም አገልግሎት እንዳያገኙ በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና አንዳንድ በፌዴራል እና በከተማ መስተዳድር ቢሮዎች ጥቁር የለበሱ እና በሐዘን ላይ ያሉ ልጆቻቸው በእሥር መንገላታታቸውን የዓይን ምስክሮች ማረጋገጣቸውን ጠቅሷል።
በድርጊቱም "ሹማምንት ስልጣናቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት መሆኑን እና ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ንቀት እና ጥላቻ ያላቸው መሆኑን ተረድተናል"ብሏል፡፡
ተገቢውን ፍትሕና ፍትሐዊ መፍትሔዎችን በአግባቡ ግብር ላይ አውለዋል ላላቸው አስተዳደሮችና ክልላዊ መንግሥታት ምሥጋናውን ቸሯል።
"በዚህ አጋጣሚ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ ሌሎች የክልል ርዕሳን መስተዳድሮችና ከተሞች በተለይም
* የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤
* የሲዳማ ክልላዊ መንግስት፣
* የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፤
* የሱማሌ ክልላዊ መንግሥት፤
* የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት፣ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣
* የአፋርና ጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤
* በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ እና ሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስናቸው መንግሥታዊ ተቋማት የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመከተል በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የወሰዳችሁ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መፍትሔዎችን እናደንቃለን፣ በቤተ ክርስቲያንም ስም እናመሰግናለን፡" በማለት።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ፤ ቤተክርስቲያኒቱ የካቲት 5 ለማከናወን ያቀደችው ሰላማዊ ሰልፍ ክልከላ መብቶችን የሚጥስ እንደሆነ ሲጠቅስሲጠቅስ "የትኛውም ሰልፍ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማድረግ አይቻልም በማለት የተደረገው ክልከላን በተመለከተም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ መሠረታዊ መብት ሆኖ የተጠቀሰ እና በሕገ መንግሥቱም አንቀፅ ፴ ላይ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ መንግሥት ራሱ የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይኖርበታል" ብሏል።
አክሎም "በደላችንን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እና መንግሥትም ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና አፈና ወጥቶ ሕግ እንዲያከብር እና እንዲያስከብር የጠራነው የየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍም መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እንድናከናውን መፍቀድ አሊያም የጠየቅናቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ እና አንድ በአንድ መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
"ቤተክርስቲያኒቱ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን እያሳወቅን መንግሥትም ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን እያሳሰብን ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑንም እናሳውቃለን" በማለት አሳስቧል።
ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥም አስታውቋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 1 ቀን ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ፤ የካቲት 2 ቀን 2015 የመግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ "በሕገ መንግሥታችን መንግሥታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግሥት ሊኖር እንደማይችል ተደንግጓል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዉስጣዊ አሠራርና ከዚያም ካለፈ በፍትሐ ብሔር ዳኝነት የሚታይ ነው" ሲል አመላክቷል።
አያይዞም፤ በቤተክርስቲያኒቱ የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለፖለቲካዊ ዓላማ ለማዋል የተሰናዱ የተለያዩ ቡድናት እንዳሉ ሲጠቅስ ""የመሥዋዕትነት ሰልፍ አዘጋጅ " በሚል ከባለ ሀብቶች፣ ከፖለቲከኞች እና ከ"መንፈሳውያን የወጣት አደረጃጀቶች" የተውጣጣ ቡድን ከማዕከል እስከ ታች መዋቀሩን መንግሥት ደርሶበታል።
"አጋጣሚዉን በትጥቅ በተደገፈ ሁከት መንግሥትን የመነቅነቅ ፍላጎት ያለው ይህ ቡድን ወጣቶችን እየመለመለ ማሠማራት መጀመሩን፣ ለዓላማዉ በልዩ ልዩ መንገዶች ገንዘብ በመሰብሰብ እያሠራጨ መሆኑንና በሕገ ወጥ መንገድ ከታጠቁ ኃይሎች ጋርም ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን መንግሥት አረጋግጧል።
ለዚሁ እኩይ ዓላማ አስቀድሞ አስቦበት ያደራጁት የሚዲያ ቡድን ሥራዉን መጀመሩም ተረጋግጧል" ብሏል፡፡
መግለጫው አያይዞም "ከዚህ በኋላ መንግሥት ቀደም ሲል ሲገልፅ እንደ ነበረዉ ጉዳዩ ቀይ መሥመር ያለፈ ሆኖ በማግኘቱ፣ “የመሥዋዕትነት ሰልፍ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ የሌለ በመሆኑ ሀገራዊ መረጋጋትን ለመፍጠርና የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል መንግሥት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ዉስጥ የሚገባ መሆኑን ከወዲሁ ያሳዉቃል" ሲል ማስጠንቀቂያ ያዘለ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።