የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ዛሬ እሑድ ጳጉሜን 5 መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ለኢትዮጵያውያን ብሥራተ ዜናቸውን "በእንኳን ደስ አላችሁ" የገለጡት ጠቅላይ ሚኒስትር የአራቱን ዙር የግድብ ሙሌት ሂደት በምልሰት አንስተው "ብዙ ፈተና ነበረው፤ ወደኋላ እንድንመለስ ብዙ ተጎትተን ነበር። በውስጥ ፈተና በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል።" ብለዋል።
አክለውም "ለግድቡ የምናደርገውን ማናቸውንም ድጋፍ እስከ ፍጻሜው እንድንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ አደራ እላለሁ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቡድን 20
በኒው ዴልሂ ለ18ኛ ጊዜ ከጳጉሜን 4 እስከ 5 የተካሔደው የቡድን 20 አገራት የምጣኔ ሃብት ትብብር ጉባኤ ዛሬ ተጠናቅቋል።
ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመሩት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ናቸው።
አስተናጋጇና የጉባኤው ሰብሳቢ አገር ሕንድ የአረንጓዴ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስና ሕይወት፣ ቴክኖሎጂያዊ ሽግግርና የዲጂታል ሕዝባዊ መሠረተ ልማት፣ የ21ኛ ክፍለ ዘመን ዘርፈ ብዙ ተቋማትና ሴቶች- መር ልማትን አክሎ ስድስት ዋነኛ የመወያያ አጀንዳዎች ለውይይት አቅርባለች።
በጉባኤው ሂደት ወቅት የአፍሪካ ሕብረት ሙሉ የቡድን 20 አባል መሆኑ ይፋ ተደርጓል።
ጉባኤው ባወጣው የጋራ ማጠቃለያ መግለጫው የዩክሬይንና ሩስያን ጦርነት አስመልክቶ ጦርነቱ "በእጅጉ ብርቱ ሰብዓዊ ሰቆቃን" አስከትሏል "ሁሉም መንግሥታት ከስጋት ፈጣሪነተንዲቆጠቡ" እና "ዘመኑ የጦርነት ዘመን ሊሆን አይገባም" ሲል ሩስያን ነጥሎ ከማውገዝ ተቆጥቧል።
ሆኖም፤ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ የቡድን 20 የጋራ መግለጫ የዩክሬይንን ጦርነት በማውገዝ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፏል በማለት ተናግረዋል።
የሁለቱን ቀናት ጉባኤ ለማካሔድ ሕንድ 120 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ አድርጋለች።
ሕንድ ለቀጣዩ የቡድን 20 አስተናጋጅ አገር ብራዚል የሰብሳቢነት ኃላፊነት አስረክባለች።