የተባበሩት መንግሥታት ኤጄንሲዎችና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ከ750 ሺህ በላይ ስደተኞች ቀለብ ለመስፈር ለ73 ሚሊየን ዶላር አስቸኳይ እርዳታ አቤት አሉ።
አስቸኳይ እርዳታ ጠያቂዎቹ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ናቸው።
በምግባረ ሰናይ ድርጅቶቹ ማሳሰቢያ መሠረት የዓለም ምግብ ድርጅት ኦክቶበር ላይ ለስደተኞች የሚያቀርበው ምግብ አይኖረውም።
ለኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይና ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር "አስቸኳይ የገንዘብ ድጎማ ካላገኘን የአንድ ሚሊየን ሶስት አራተኛ ስደተኞች በሳምንታት ዕድሜ ውስጥ ቀለብ አልባ ይሆናሉ" ሲሉ የተማፅኖ ማስጠንቀቂያ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የምግብና እርሻ ድርጅት ከተመድ ማዕከላዊ የአስቸኳይ ድጎማ ግብረምላሽ ለትግራይ ገበሬዎች የማዳበሪያ አቅርቦቱን ከፍ ማድረጊያ የ10 ሚሊየን ዶላር ብድር አግኝቷል።
ፈጣን የብድር አቅርቦቱን አስመልክቶም የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ንዑስ ሪጂን አስተባባሪና ለኢትዮጵያ ጊዜያዊ ተወካይ ዲቪድ ፊሪ ለለጋሽ ድርጅቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አክለውም፤ ገበሬዎቹ የሚያሹትን ግብዓት በወቅቱ ካገኙ ለማምረትና ምርታቸውንም ከኦክቶበር 2022 ጀምሮ ለመጠቀም እንደሚችሉና ምርቱም ቢያንስ ለስድስት ወራት ፍላጎታቸውን ሊሸፍን እንደሚያስችላቸው አመላክተዋል።