ቻይና በተኩስ የታጀበ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ማብቃቷን አስታወቀች።
የወታደራዊውን እንቅስቃሴ ማክተም ያስታወቀው የቻይና ምሥራቅ ዕዝ የወታደሮቹን የውጊያ ብቃት "በብርቱ ፈትኖ" ያበቃ በመሆኑ የጦር ልምምዱን መግታቱን ገልጧል።
የታይዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግና ቻይና ያካሔደችው የጦር ልምምድ ደሴቲቱን ለመውረር የተካሔደ የጦር ዕቅድ መሰናዶ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር ሺኦ ችየን በበኩላቸው ቻይና ከታይዋን ጋር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመዋሃድ የምትሻ መሆኑን ትናንት በአውስትራሊያ ብሔራዊ ፕሬስ ክለብ ባደረጉት ንግግር አመላክተዋል።
***
የኬንያ ፖሊስ በመዲናይቱ ናይሮቢ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የድምፅ ማጭበርበር ጥርጣሬ ክስ ደርሶት ባካሔደው ፍተሻ ሳቢያ የማቱጋ ምርጫ ጣቢያ በጊዜያዊነት እንዲዘጋ ተደርጓል።
ፖሊስ በሥፍራው ደርሶ ባካሔደው ፍተሻ ሁለት ግለሰቦች ሕጋዊ ያልሆኑ አንድ የኤሌክትሮኒክስ ድምፅ መቁጠሪያ፣ የምርጫ ኮሚሽን ማኅተምና ድምፅ ያልተሰጠባቸውን የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ይዘው ተገኝተዋል።
ሁለቱ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ወደ ኪዋሊ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
በመሪነት ላይ በሚገኙት ሁለት ዕጩ ፕሬዜደንቶች ራይላ ኦዲንጋና ዊሊያም ሩቶ መካከል ተቀራራቢ ውጤቶች በኬንያ ዋነኛ ብዙኅን መገናኛዎች እየተገለጡ ነው። ሆኖም የውጤት መግለጫዎቻቸው የተለያዩ ናቸው።

Kenya's Deputy-President and Presidential candidate for Kenya first, William Ruto (L) and, One Kenya Coalition Party presidential candidate Raila Odinga (R). Credit: SIMON MAINA/AFP via Getty Images) / Ed Ram/Getty Images
የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ሐሙስ ጠዋት የቅድሚያ ምርጫ ውጤት ሪፖርቱን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጧል።