የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በገጠማት ችግር ለእሁድ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. የጠራችውን ሰላማዊ ሰልፍ እንዲራዘም ወሰነች።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባን ተከትሎ በተሰጠው መግለጫ መንግሥት የቀረቡለትን ጥያቄዎችን ለመመለስ በመወሰኑ ሰልፉ መራዘሙ ተገልጧል።
"ሰልፉ እንዲራዘም የተወሰነው ቤተ ክርስትያኗ የአቋም ለውጥ አድርጋ ሳይሆን ለሰላም ክፍት በተደረገው በር መንግስት ችግሩን ለመፍታት በመስማማቱ ነው" ተብሏል።
መግለጫው አያይዞም "ነገር ግን መንግሥት የገባውን ቃል እና የወሰነውን ውሳኔ የማይፈፅም ከሆነ መንፈሳዊ ተጋድሏችን የሚቀጥል ይሆናል" ሲል አሳስቧል።
በማከልም ሰልፉ በተጠራበት ዕለተ እሑድ የካቲት 5 ቀን የእምነቱ ተከታዮች በየአጥቢያቸው በሚገኙ ዐቢያተ ቤተክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ላይ ባለመቅረት የተለመደውን የዕለተ ሰንበት የሥርዓተ ቅዳሴ፣ የጸሎት፣ የምሕላና የትምህርት ወንጌል ከወትሮው በተለየ የመንፈሳዊ ሥርዓት በማከናወን እንዲያሳልፉ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ ማስተላለፉን ጠቅሷል።
በፌዴራል መንግሥቱና በቤተ ክህነት መካከል በተካሔደው ውይይት ላይ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ የተመራ አሥራ ሁለት ብፁዓን ሊቀ ጳጳሳት፣ በመንግሥት በኩል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች መገኘታቸውም ተጠቅሷል።
መግለጫው በውይይቱ ላይ የተነሱ ነጥቦችን ሲያመላክት "በዋነኛነት ቤተ ክርሲቲያን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ጠብቃ የምትሰራና ከዚህ ውጪ ምንም ዓይነት ድርድር የሌለው መሆኑን ገልፃለች። በዚህም መነሻ መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል ወደፊትም የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሉዓላዊነት በጠበቀ መንገድ እንደሚሠራ አረጋግጧል" ብሏል።