ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ዛሬ ጥር 4 ፓፕዋ ኒው ጊኒ ተገኝተው የሁለትዮሽ የፀጥታ ስምምነት ፊርማ ያኖራሉ።
አቶ አልባኒዚ በታሪካዊነቱ የመጀመሪያው የውጭ አገር መሪ በመሆንም ለፓፕዋ ኒው ጊኒ ፓርላማ ንግግር ያሰማሉ።
በንግግራቸውም የሁለቱን አገራት ፀጥታ ደረጃ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ትምህርት፣ ባዮሴኩሪቲና መሠረተ ልማት ዙሪያ ያለውን ትብብር ከፍ ስለማድረግ እንደሚያነሱ ከወዲሁ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የስደተኞች መብቶች ተሟጋቾች ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒዚ ፓፕዋ ኒው ጊኒ ውስጥ ያሉ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሙሉ ከዚያ እንዲያስወጡ ጠይቀዋል።
በ2013 ማኑስ ደሴት ከነበሩ ከከ1,000 በላይ ጥገኝነት ጠያቂዎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት 90 ጥገኝነት ጠያቂዎች ፓፕዋ ኒው ጊኒ ውስጥ ይገኛሉ።
በርካቶቹም ለአዕምሮ ሕመምና ለአካላዊ ጤንነት መታወክ ተጋልተው ያሉ መሆናቸውንም የስደተኞች መብቶች ተሟጋቾቹ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒዚ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ፓፕዋ ኒው ጊኒ ገብተዋል።
ሩስያ
ሩስያ የዩክሬይንን ጦርነት የሚመሩ አዲስ ጄኔራል ሾመች።
ቀደም ሲል የዩክሬይን ጦርነትን እንዲመሩ ሾማቸው የነበሩትን ጄኔራል ሰርጌይ ሱሮቪኪን ከሶስት ወራት የአመራር ኃላፊነት በኋላ በጄኔራል ቫሌሪ ገራሲሞቭ መተካቷን የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አክሎም ከዋና አዛዥነታቸው የተነሱትና ከኪኸርሰን ያፈገፈጉት ጄኔራል ሱሮቪኪን በምክትል አዛዥነት እንደሚቀጥሉ ገልጧል።