የአልባኒዚን መግሥት የጡረታ አበል ተቀማጭ የታክስ ረቂቅ ድንጋጌ ተከትሎ 544 ሚሊየን ዶላር የጡረታ አበል ተቀማጭ ያለው ግለሰብ ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስቶ ቢሊየነሮችንና የታክስ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
አውስትራሊያውያኑ ቢሊየነሮች ጂና ራይን ሃርትና ዲክ ስሚዝ "እኛ የለንበትም፤ የእኛ ተቀማጭ አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚም ፓርላማ ውስጥ ባካሔዱት ንግግር "ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ የጡረታ አበል ተቀማጭ ያለውን ግለሰብ ማንነት የሚያውቅ አንድ አውስትራሊያዊ ቢኖር የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን ብቻ ነው" ሲሉ በሽሙጥ ተናግረዋል።
እንደ አውስትራሊያ የጡረታ አበል ማኅበር ሪፖርት በ2019 የፋይናንስ ዓመት 27 የጡረታ አበላቸውን በግል የሚከውኑ ግለሰቦች ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ የጡረታ አበል ተቀማጭ አላቸው።
ለዳታው ስርጭት አስባብ የሆነው የፌዴራል መንግሥቱ የጡረታ አበል ተቀማጫቸው ከ3 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ ግለሰቦች ከ2025 ጀምሮ አሁን ከሚከፍሉት 15 ፐርሰንት ተጨማሪ 15 ፐርሰንት በማከል ለመንግሥት 30 ፐርሰንት ታክስ እንዲከፍሉ ረቂቅ ድንጋጌ መዘጋጀቱን ተከትሎ ነው።
በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ ፕሮፌሰር ሱዛን ቶርፕ፤ አንድ ግለሰብ የ$544 ሚሊየን ዶላር የጡረታ አበል ተቀማጭ ላይ ለመድረስ ለ50 ዓመታት በስምንት ፐርሰንት ስሌት በዓመት $1 ሚሊየን ዶላር ያህል ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
አክለውም፤ አሁን ባለው የጡረታ አበል ተቀማጭ ገደብ ይህን ያህል ተቀማጭ ማድረግ እንደማይቻልና ምናልባትም ገደቦች ላልተው በነበረበት ወቅት ያን ያህል ገንዘብ ማስቀመጥ ወይም ማሸጋገር ተችሎ ይሆናል ሲሉ ግምታቸውን ገልጠዋል።
ሞዛምቢክ
ሳይክሎን ፍሬዲ የደቡብ አፍሪካዊቷን አገር ሞዛምቢክ ዳግም አጥቅቷል።
ሳይክሎን ፍሬዲ ከሳምንታት በፊት ሞዛምቢክ ላይ በእጅጉ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል።
በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ለአደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። ንግዶች ተዘግተዋል፣ በረራዎች ተገትተዋል፤ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የኤሌክትሪክ ስርጭቶች ተቋርጠዋል።
የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች የሳይክሎኑ ከ34 ቀናት በኋላ ማዝገምን ማሳየት እርጥበትን በማምጣት ከባድ ዝናብን ሊያስከትል እንደሚችል አመላክተዋል።
ባለፈው ወር ሳይክሎኑ ሞዛምቢክን ባጠቃበት ወቅት 171 ሺህ ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል።
በተባበሩት መንግሥታት መግለጫ መሠረት 27 ሞዛምቢካውያንና 17 የማዳጋስካር ዜጎች በሳይክሎኑ ጥቃት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።